ኢትዮጵያ ለእዳ ክፍያ 463 ቢሊዮን ብር መመደቧ ተገለጸ

የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ፣ ለ2018 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ወይም 14 ቢሊዮን ዶላር ረቂቅ የፌደራል በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

ረቂቅ በጀቱ እየተጠናቀቀ ካለው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ31 በመቶ ብልጫ ያለው ነው።

ከቀረበው ረቂቅ በጀቱ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ፣ 415 ቢሊዮኑ ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊዮኑ ለክልሎች ድጎማና 14 ቢሊዮኑ ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እንዲውል መመደቡን ሚንስትሩ አብራርተዋል።

ከጥቅል አገራዊ ምርት አንጻር 2 ነጥብ 2 በመቶ ያልተጣራ የበጀት ጉድለት ያጋጥማል ተብሎ እንደሚጠበቅና ኾኖም መንግሥት ጉድለቱን ለመሙላት ከብሄራዊ ባንክ ብድር እንደማይበደር ተገልጧል።

ይህ በዚህ እንዳለ መንግስት ከያዘው በጀት አንድ ሶስተኛውን ለእዳ ክፍያ መያዙ ተገልጿል።

በፌዴራል የመደበኛና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ከያዙት ውስጥ ለእዳ ክፍያ አንድ ሶስተኛው ወይም 463 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ( 29 በመቶ) ወይም 3.4 ቢሊዮን ዶላር በመያዝ ቀዳሚ ሲሆን በመቀጠል ለመጠባበቂያ 269 ቢሊዮን ብር (16.8 በመቶ) እንዲሁም በሶስተኛነት ለበጀት ድጋፍ 216 ቢሊዮን ብር (13.5 በመቶ) ተይዟል።

ከረቂቅ በጀቱ 1 ትሪሊዮን ብር ወይም 73 በመቶውን ከታክስ ገቢ 236 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች ቀሪውን ደግሞ ከፕሮጀክቶች ድጋፍ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች ለማግኘት መታቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ገልፀዋል።

መንግስት የበጀት ጉድለቱን በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ ብድር በመውሰድ ሳይሆን በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ እንደሚሸፍን ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ጥብቅ የገንዘብ እና የበጀት ፖሊሲን በመከተል የመንግስት ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ይህም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምን ለመተግበር የሚያስችል መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የ2018 ረቂቅ በጀት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን እና የ10 ዓመቱን መሪ የልማት እቅድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት የ8.9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚጠበቅም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *