በጋምቤላ ክልል ባለሀብቶች ህጻናትን በከብት እየለወጡ ነው ተባለ

በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳን ሙርሌ ብሄረሰብ ታፍነው ለባርነት የሚወሰዱ ህፃናት መኖራቸውን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው  የሕገ ወጥ ዝውውር ጽህፈት ቤት  አሰተባባሪ አቶ ኡቶው ቹሩ  እንደተናገሩት በዚህ መልኩ የሚወሰዱ ህፃናትን የማስመለስ ስራ ሲሰራ ቢቆይም ህገወጥ የህፃናት ዝውውርን ማስቀረት አልተቻለም ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን በኩል ያለው ድንበር  ክፍት መሆን በክልሉ ያሉ እና እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ህፃናትን በህገወጥ መልኩ ለመውሰድ አመቺ እንዳደረገው ገልፀው ባለሀብቶች ህፃናቱን በከብት የሚለውጡበት ሁኔታ መኖሩም ድርጊቱን እንዳይቆም ማድረጉን ተናግረዋል።

አኙዋክ ብሔረሰብ ዞንን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች በደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ህፃናቱ እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከተወሰዱት ውስጥ በቅርቡ ሶስት ህፃናትን ማስመለስ መቻሉን የገለፁት አቶ ኡቶው በህይወት መኖራቸው ያልተረጋገጡ አራት ህፃናት እንዳልተመለሱ ተናግረዋል።

ቢሮው  ችግሩን ለመፍታት  ከዩኒሴፍ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ህገ-ወጥ የህፃናት ዝውውርና ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ሲሰራ ቢቆይም የበጀት እጥረት አሉታዊ ጫናን ፈጥሮበት እንደነበር አስታውሷል።

ችግሩ በተለይም እንደ ዲማ ባሉ ወረዳዎች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ አስተባባሪው በመግለፅ የህፃናቱን ተጋላጭነት ለመቀነስ በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በሚገባ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች፤ በጋምቤላ ክልል፣ በአኙክ ዞን፣ ዲማ ወረዳ በሚገኝ ቦታ ላይ በከፈቱት “የደፈጣ ተኩስ ጥቃት” ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው የአስተዳደር እና የፖሊስ ኃላፊዎች መናገራቸው ይታወሳል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃቱን የሰነዘሩት፤ ከዲማ ወረዳ 39 ሰዎች አሳፍሮ ወደ ጎግ ወረዳ ሲጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ እንደሆነ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ኡታክ ሜዶ ተናግረዋል።

የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሱ የደፈጣ ጥቃት የተሰነዘረበት፤ ከዲማ ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ አቻኛ እና 45 በተባሉ ቀበሌዎች መካከል በደረሰበት ወቅት እንደሆነ የፖሊስ አዛዡ በወቅቱ አስረድተዋል።

ታጣቂዎቹ በአውቶብሱ ላይ ተኩስ በከፈቱበት ወቅት “መሳሪያ የያዘ ተሳፋሪ” መልሶ በመተኮስ አጸፋውን መመለሱን ረዳት ኢንስፔክተር ኡታክ አመልክተዋል። በተኩስ ልውውጡ አንድ ታጣቂ መገደሉንም የፖሊስ አዛዡ ጠቁመዋል። በታጣቂዎቹ የደፈጣ ጥቃት የአውቶብሱን ሹፌር ጨምሮ የስድስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ከአንድ ወር በፊት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል የገቡ ታጣቂዎች የቀበሌ አመራር ላይ ተኩሰው ማቁሰላቸው ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *