ኢትዮጵያ የጣና ደሴት እና ገዳማትን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ዘመቻ ጀመረች

የጣና ሀይቅ ደሴትና ገዳማት በአለም አቀፍ የቅርስ መዝገብ እንዲሰፍሩ የሚያስችለዉ ሰነድ ለዮኔስኮ ተልኳል።

በአማራ ክልል የሚገኙ የመስህብ ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የባህልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማሳደግ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ  አስታውቋል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ እምቢአለ እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ በርካታ የመስህብ ቦታዎች እንደመኖራቸው የጣና ሀይቅ እና አካባቢውን በዮኔስኮ አለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ከዚህ ቀደም  የጣና ሀይቅ ደሴቶች በብዛ ህይወት ቅርስነት የተመዘገበ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት ይህ ስፍራ በአለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማድረግ በተዘጋጀዉ ሰነድ ዙሪያ ማስተካከያ መደረጉን ተናግረዋል።

ሰነዱን አስመልክቶ አስተያየት የመስጠትና ተጨማሪ ግብዓቶችና ማስተካከያዎችን የማዘጋጀት ስራ ሲሰራ እንደቆየ የገለፁት አቶ አበበ ይህ ሂደት በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቢሮው ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ጋር በመሆን የጣና ገዳማትንና ባህረ ደሴትን እንዲሁም ረግረግ መሬቶችን በአለም አቀፍ የቅርስነት መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍሩ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ተገልጿል።

እንደዚሁም ስፍራው አለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በሚያስችለው በዚህ ሰነድ ዙሪያ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ ሰነዱ ለዮኔስኮ ተልኳል ተብሏል።

ዩኔስኮ አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላቱን አረጋግጦ ተቀብሎታል የተባለ ሲሆን ውሳኔውን በቀጣይ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 11 ቅርሶችን በዩኔስኮ መዝገብ ስር በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሲሆን ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካን በመብለጥ በአንደኝነት ትመራለች።

ደቡብ አፍሪካ 10 ቅርሶችን ስታስመዘግብ ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ዘጠኝ ቅርሶችን በዩኔስኮ ስታስመዘግብ ቱኒዝያ ስምንት እንዲሁም ግብጽ፣ ሴኔጋል እና ታንዛኒያ ደግሞ ሰባት ቅርሶችን ያስመዘገቡ ሀገራት ናቸው።

ከሁለት ዓመት በፊት ዩኔስኮ ዓመታዊ ጉባኤውን በሳውዲ አረቢያ መዲና ሪያድ ባካሄደበት ወቅት ሁለት የኢትዮጵያ ጥብቅ ስፍራዎችን በዓለም የብዝሀ ሀብትነት መዝግቧል።

የጌድኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር እና የባሌ ብሔራዊ ፓርክ በዕጽዋዕት፣ ፍራፍሬ እና በሰብል ምርቶች ታዋቂነትን ያተረፉ የብዝሀ ህይወት ማዕከላት ሲሆኑ ዩኔስኮም በዓለም ብዝሀ ህይወት ሀብትነት መዝግቧቸዋል።

ኢትዮጵያ ይህን ቅርስ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ላለፉት 10 ዓመት በይፋ አመልክታ ክትትል ስታደርግ እንደነበር በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *