በትግራይ ክልል 259 ሰዎች በፈንጅ መገደላቸው ተገለጸ

በትግራይ ክልል ባለፈው ሁለት አመት 1664 ሰዎች በተቀበሩ ፈንጂዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈፀመ ወዲህ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው ከእነዚህ ውስጥ 259ኙ ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ የክልሉ መልሶ ግንባታና ልማት ድርጅት (ራዶ) አስታውቋል፡፡

አለም አቀፍ የፈንጂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን ምክንያት በማድረግ በመቀሌ በተደረገ ስብሰባ ላይ የክልሉ መልሶ ግንባታና ልማት ድርጅት ሀላፊው አቶ ተስፋይ ገብረማሪያም እንደገለፁት የተቀበሩ ፈንጂዎችና ጥይቶች አሁንም በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የፈንጂ አምካኝ ግብረ ሀይል አስተባባሪ የሆኑት ኮሎኔል ተስፋይ አብርሀ በበኩላቸው በክልሉ ውስጥ በየቀኑ የፈንጂ አደጋዎች እየደረሱ መሆናቸውን ገልፀው የበጀት እጥረትና ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አለመስጠት ስራቸውን እያደናቀፈባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት ትግራይን እያስተዳደረ ያለው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳድር እንደ አዲ እየተዋቀረ ይገኛል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነት የነበሩት ጌታቸው ረዳ በጄኔራል ታደሰ ወረደ ከሰሞኑ መተካታቸው ይታወሳል፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚህ የስልጣን ርክክብ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል፡፡

ጀነራል ታደሰ ወረደ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ መልሶ ማቋቋም፣ በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ፤ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤ ለዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡

እንዲሁም መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲሣለጡ ማድረግን ጨምሮ ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር_ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎችን አስቆማለሁ ብለዋል፡፡

ክልሉ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፤ በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና  የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ደሞክራሲያዊ ዐውድ እንዲፈጠር ለመሥራትም ቃል ገብተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ_የምክክር_ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትሥሥር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናከሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በስልጣን ርክክቡ ወቅት ቃል ገብተዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ማድረጉ ይታወሳል።

ሚኒስቴሩ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተካሄደው ጦርነት የደረሰውን ጉዳትና የመልሶ ግንባታ ፍላጎትን አስመልክቶ ባደረገው ጥናት የጦርነቱ አጠቃላይ ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል።

ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በጦርነቱ በቀጥታ የተጎዱ ሲሆን ሦስት ሚሊዮን ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት የከፋ ድህነት ውስጥ ገብተዋል ተብሏል።

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተቀመጠው የጉዳት መጠን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከውጭ አበዳሪዎች ለኢኮኖሚ ልማት ተበድራ ካልመለሰችው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ጋር እኩል ሆኗል።

በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *