የእስራኤል አምባሳደር ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ላይ በአፍሪካ ህብረት ተባረሩ
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አብርሃም ንጉሴ፣ ዛሬ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን ለማስታወስ በተካሄደው 31ኛዉ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት እንዲወጡ ተደርጓል።
ይህ የሆነው በርካታ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት አምባሳደሩ በዚሁ የሐዘን ስነ-ስርዓት ላይ መገኘታቸውን በመቃወማቸው መሆኑ ተዘግቧል ።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኦረን ማርሞርስቴይን ድርጊቱን “አሳፋሪ” እና “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ በጽኑ አውግዘዋል።
“በአዲስ አበባ የሚገኘው የእስራኤል አምባሳደር በተጋበዙበት፣ በሩዋንዳ የቱትሲ የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን ለማስታወስ በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ፀረ-እስራኤላዊ የፖለቲካ አመለካከቶችን ማስተዋወቃቸው እጅግ አሳፋሪ ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ማርሞርስቴይን አክለውም፣ “ይህ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በመጀመሪያ ደረጃ የተገደሉትን ትውስታ የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ የሩዋንዳ ህዝብን እና የአይሁድ ህዝብን ታሪክ መሠረታዊ ግንዛቤ ማጣቱን ያሳያል።”
የእስራኤል ሚዲያ የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሰዉ እንደዘገቡት ይህ ክስተት በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የእስራኤልን አቋምና ከአባል ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ያለውን ቀጣይ ውጥረት የሚያሳይ ነው ሲሉም አስፍረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ በነበረበት የካቲት 2023 ላይ በተመሳሳይ የእስራኤል ልኡክ ከስብሰባው መባረራቸው ይታወሳል።
የአፍሪካ ህብረት በወቅቱ የእስራኤል ዲፕሎማቶችን ያባረረው እስራኤል በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንድትካፈል አልተጋበዘችም በሚል ነበር።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት በሰሩት ሴራ ምክንያት ህብረቱ የእስራኤል ዲፕሎማቶችን አባሯል ሲል ድርጊቱን ተችቶም ነበር።