የአዲስ አበባ ባለሀብቶች ያላመኑበትን ግብርና ታክስ በተጨማሪ በሌሎች ችግሮች እየተፈተኑ እንደሚገኙ ተገለፀ
የአዲስ አበባ ባለሀብቶች ፎረም በከተማው ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶች ከባድ ችግሮች እያጋጠሟቸው መሆኑን ገልጿል። ፎረሙ የባለሀብቶችን ቅሬታ በሰነድ የተደገፈ መረጃ ለመቀበል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የባለአብቶች ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ሙሴ አያሌው ለካፒታል እንደገለጹት፣ ባለሀብቶቹ ያላግባብ ድርጅቶቻቸው መታሸግ፣ መፍረስ፣ መነጠቅ (መቀማት)፣ ሥራ እንዲያቆሙ መደረግ፣ ያላመኑበትን ከፍተኛ ግብርና ታክስ ለማስከፈል ማስገደድ፣ የባንክ አካውንታቸው መታገድ፣ ከሀገር እንዳይወጡ ወይም እንዳይገቡ እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በስልክ ዛቻና ማስፈራሪያ ማድረስ፣ የማያምኑበትን አሰልቺና ተደጋጋሚ መዋጮዎች መጠየቅ፣ እንዲሁም ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይከውኑ ማዋከብ፣ የብድር አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ያለማግኘት እና የመሳሰሉት ችግሮች እየደረሱባቸው መሆኑን ሰምተናል ብለዋል።
ይህን ተከትሎ ፎረሙ ከመጋቢት 01 እስከ 27 ቀን 2024 ዓ.ም ድረስ የከተማውን ባለሀብቶች ቅሬታ በሰነድ የተደገፈ መረጃ ለመቀበል መዘጋጀቱንና ባለሀብቶችም መረጃቸውን በሰነድ በማቅረብ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
የባለሀብቶቹ ቅሬታ ከተሰበሰበ በኋላ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ችግሮቹ እንዲፈቱ ፎረሙ እንደሚሰራ አቶ አሸናፊ ሙሴ አያሌው ለካፒታል ጋዜጣ ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ዕዳ ያለባቸው 62 ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የግብር ዕዳ ያለባቸውና በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ዕዳቸውን ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ 62 ግለሰቦችን ላይ ነው ትዕዛዙ የተላለፈው::
በዚህም ቢሮው በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ ከ1-3 ለተቋሙ በተሰጠ ስልጣን መሰረት ከሀገር እንዳይወጡ ለፌዴራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዝርዝራቸውን ማስተላለፉን አሳውቋል፡፡
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የግብር ዕዳቸውን በአግባቡ ሳይወጡ የሚሰወሩ ግብር ከፋዮችን በመከታተል ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የዕዳ ክትትልና አስተዳደር የስራ ክፍልን በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቋል::
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ሲል ቢሮው ጥሪውን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡