የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂስፓሻል ኢኒስቲትዩት እንደገለጸው በፈረንጆቹ 2026 ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ በሥራ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ቀጣይ ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ ታመጥቃታለች የተባለው ሶስተኛ ሳተላይት ከዚህ ቀደም መጥቀው አገልግሎት ጊዜያቸው ካበቁት ሁለት ሳታላይቶች የተሻለ የምስል ጥራት ይኖራታል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ ከቻይና መንግስት ጋር ተፈራርማ እየሰራች መሆኑን የነገሩን በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት የሳተላይት ክትትል ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ፉፋ ናቸው፡፡
አቶ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ሶስተኛዋን እና የተሻለ የመሬት ምልከታ ጥራት ያላትን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ ስራ መጀመሯን አስረድተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማልማት በምን ያክል ገንዘብ ከቻይና ጋር እንደተዋዋለ አልተናገረም፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ያመጠቀቸው በ2012 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ነበር፡፡
የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች የተፈጥሮ አደጋን አስቀድሞ ለመተንበይ፣ የጎርፍ እና የአየር ንብረት ለውጥን አስቀድሞ ለመረዳት ያስችላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ETRSS-02 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በ2023 ላይ እንደምትመጥቅ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም መራዘሙ ተገልጿል፡፡
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሶስት ወራት በፊት በሰጠው መግለጫ በቅርቡ ሶስተኛዋን ሳተላይት አመጥቃለሁ ሲል ገልጾ ነበር፡፡
ከዚህ በፊት በቻይና አጋዥነት ወደ ሕዋ የመጠቁት ሳተላይቶች የተቀመጠላቸውን የአገልግሎት ጊዜ በመጨረስ ተልዕኳቸውን በስኬት ማጠናቀቃቸውም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።