በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የኮንዶም እጥረት ለመቅረፍ የግል የመድሃኒት አስመጪዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ጥሪ እየቀረበ ነው፡፡
በየዓመቱ በመንግስትና በግብረሰናይ ድርጅቶች ከ90 ሚሊዮን ያልዘለለ አቅርቦት ቢኖርም ዓመታዊ ፍላጎቱ ግን 270 ሚሊዮን ይደርሳል፤ ቀድሞውንም ቢሆን እጅግ የተራራቀ አቅርቦትና ፍላጎት ያለበት ኮንዶም አሁን ደግሞ የአሜሪካ መንግስት የተራድኦ ድርጅት የሆነው ዩኤስ አይዲ የሚሰጠውን ድጋፍ ማገዱ እጥረቱን አባብሶታል፡፡
ከዚህ ቀደም በነፃ ይታደል የነበረው፣አልፎ አልፎም በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በየሱቁ ይገኝ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የአንድ ኮንዶም አማካኝ ዋጋው 50 ብር ደርሷል፡፡
እንደ ጋምቤላ ባሉ የክልል ከተሞች እጥረቱን ተከትሎ በተፈጠረ የዋጋ ንረት አንድ ኮንዶም እስከ 250 ብር እተሸጠ መሆኑን ተነግሯል፡፡
በዚህና በሌላውም ምክንያት ኮንዶምን የመጠቀም ዝንባሌ መቀነስ ማሳየቱ የኤች አይቪ መከላከል ስራውን ፈታኝ እንዳያደርገው ስጋት እንዳለው በዘርፉ ከሚሰሩት ተቋማት መካከል የሆነው ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን ተናግሯል፡፡
የኤ ኤች ኤፍ የመከላከልና አፍሪካ ዩኒየን ላይዘንና አድቮኬሲ ማናጀር አቶ ቶሎሳ ኦላና ድርጅታቸው እጥረቱን ለመሸፈን የግል የመድሃኒት አስመጪዎች ኮንዶምንም እንዲያስመጡ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ስራዎችን መጀመሩን ነግረውናል፡፡
ባለፈው ዓመት ሃምሌ ወር በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከኮንዶም ላይ 50 በመቶ የደረሰ የታክስ ቅነሳ የተደረገ በመሆኑ የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ ነው የሚሉት አቶ ቶሎሳ የግል የመድሃኒት አስመጪዎች ይህንን እድል ተጠቅመው ወደ ስራው እንዲገቡ የማስተባበር ስራ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
እጥረቱ በዚህ ከቀጠለ በተለይ የቫይረሱ ዝርጭት ከፍ ብሎ በሚታይባቸው አፍላ ሴት ወጣቶች ላይ ከዚህም በላይ እንዲጨምር ምክንያት ሊሆን ይችላል፤በሌሎችም ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና ሰልጣኞች በሚገኙባቸው ተቋማት በመንግስት በነፃ የሚቀርበው ኮንዶም በጣም እየቀነሰ በመምጣቱ የመከላከል ስራው ላይ እንቅፋት እንዳይሆን ስጋት ፈጥሯል፡፡
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ከዩኤስኤድ ጋር ሲሰሩ እንደነበር እና ውሳኔው ከባድ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ከ5 ሺህ በላይ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በአባልነት የያዘው የዚህ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ለአል ዐይን እንዳሉት በዩኤስኤይድ ላይ የተላለፈው የ90 ቀናት ውሳኔ ከምንም በላይ ድንገተኛ መሆኑ ጉዳቱን የከፋ እንደዳደረገው ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከሆነ በርካታ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች እየሰሯቸው የነበሩ እና ሊሰሯቸው ያቀዷቸው የሰላም፣ ጤና፣ ማህበራዊ እና ሌሎችም ስራዎች በውሳኔው ምክንያትን አስተጓጉሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እስከ 150 ሰራተኞች የነበሯቸው እና ከዩኤስኤይድ የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን አሰናብተዋል የሚሉት አቶ አህመድ ውሳኔው ተጀምረው የነበሩ በርካታ ስራዎች ማስቆሙን ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ መንግስት የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርግ እንፈልጋለን ያሉት አቶ አህመድ እገዳው በግጭት ውስጥ ባለሀገር የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ቢያንስ ድጋፉ እንዲቀጥል የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ በዩኤስ አይዲ ድንገተኛ ውሳኔ ምክንያት ከ85 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራ ማቆማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በኢትዮጵያ ካሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከ85 በመቶ በላይ ያህሉ በዩኤስ አይዲ ጥገኛ ሲሆኑ ድጋፉ በመቆሙ የቤት ኪራይ፣ የሰራተኛ ደሞዝ ጭምር መክፈል እንዳቃታቸውም ተገልጿል።