ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ለሚነሱ ችግሮች ማዕከል ነች ስትል ኤርትራ ገለጸች

ኤርትራ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ለቀረበባት ክስ ምላሽ ሰጥታለች።

የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የተነሱትን ነጥቦች አጣጥለዋል።

ሙላቱ ከሁለት ቀናት በፊት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ግጭት እንዳይከፈት ለማስቆም ጊዜው አሁን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

“ጦርነት የኤርትራ መንግስት ዋናኛ ቢዝነስ ነው” የሚሉት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች መሳተፋቸውን በጽሁፋቸው አብራርተዋል።

የትግራዩን ጦርነት “እንደ እድል በመጠቀም”ም ወታደሮቻቸውን ወደ ክልሉ አስገብተው “ውድመት” ማስከተላቸውን በመጥቀስ፥ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ “መሰናክል” ፈጥሯል ሲሉም ያትታሉ።

ፕሬዝዳንቱ ተጽዕኗቸውን የሚያሰፉት በግጭት በመሆኑ ሰላም እንቅፋት ይሆንባቸዋል፤ በትግራያ ክልል ማቆሚያ የሌለው ግጭት እንዲኖር ይፈልጋሉ፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት ደስተኛ ካልሆኑ የህወሃት አመራሮች ጋር እየሰሩ ነው በማለትም ከሰዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት የግል አስተያየት ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ የሚከሰት ችግር ለቀጠናው ስለሚተርፍ አለማቀፉ ማህበረሰብ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ይደረግ ዘንድም ጠይቀዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ትናንት በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ለቀረቡት ክሶች ምላሽ ሰጥተዋል።

“ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ግጭት እየቀሰቀሰች ነው” በሚል በሙላቱ የቀረበው ክስ ሀሰተኛ እና በተለመደው “ጥንታዊ ፋሽን” የቀረበ ነው በሚል ውድቅ አድርገውታል። 

ከቀረቡት ክሶች በተቃራኒው ቀጠናውን ለከበቡች ችግሮች “ማዕከሏ ኢትዮጵያ ናት” ያሉት ሚኒስትሩ፥ ጥሬ ሀቁን ያሳያሉ ያሏቸውን 10 ነጥቦችም በኤክስ ገጻቸው ላይ ዘርዝረው አቅርበዋል።

ሙላቱ “ታሪካዊ ሁነቶችን አዛብተው አቅርበዋል” በሚል የከሰሱት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፥ ሀገራቸው በትግራዩ ጦርነት የተሳተፈችው “ህወሃት በኤርትራ ላይ መጠነሰፊ  ጥቃት ሊያደርስ ስለነበር እና የፌደራሉ መንግስት የድጋፍ ጥያቄ በማቅረቡ” መሆኑን አውስተዋል።

ኤርትራ ከህወሃት ጥቃት ላመለጡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መሸሸጊያ እንደነበረችና “በኢትዮጵያ የጨለማ ጊዜ ለነበራት የማይተካ ሚና በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ተሰጥቷት እያለ (በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የቀረበባት ክስ አሳፋሪ ነው” ሲሉም ወቅሰዋል።

የትግራዩን ጦርነት ለማስቆም የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት “የኢትዮጵያ መንግስት የውስጥ ጉዳይ” በመሆኑ “ኤርትራ ስምምነቱን የማደናቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የላትም” ሲሉም ክሱን ውድቅ አድርገዋል።

ኤርትራ ወታደሮቿን በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው ሉዓላዊ ድንበሯ ውስጥ እንደገና ማሰማራቷን ጠቅሰው፥ የኤርትራና ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን “በቅን ልቦና ያልተቀበሉ ወይም ግጭት ለመፍጠር ዓላማ ያላቸው አካላት” የኤርትራ ወታደሮች እንደ ባድመ ባሉ የድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ የሚሉ “ሐሰተኛ ውንጀላዎችን” እያቀረቡ ነው ብለዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ን ጽሁፍ ውድቅ ከማድረግ ባሻገር በኢትዮጵያ መንግስት ላይም ክስ አቅርበዋል። 

ባለፉት ወራት የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ “ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል” ያሉት የማነ ገብረመስቀል፥ የትንኮሳው አላማ ከተቻለ በህጋዊ ካስፈለገም በወታደራዊ መንገድ ወደቦችን እና የባህር በር የማግኘት አጀንዳን ለማሳካት ሊሆን እንደሚችልም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመውን የመግባቢያ ስምምነት “የተድበሰበሰና በቀጠናው ውጥረት መፍጠሩን ቀጥሏል” ያሉት ሚኒስትሩ፥ በአማራ ክልል የማያባራ ጦርነት መቀስቀሱም ቀጠናውን ለከበቡት ችግሮች መፍለቂያዋ ኢትዮጵያ መሆኗን ሌላኛው አመላካች ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለውስጣዊ ችግሮቿ “ኤርትራን እንደ ማምለጫ መንስኤ” መጥቀሷን ከቀጠለች መፍትሄ አታገኝም ሲሉም በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የቀረበውን ክስ ተከላክለዋል።

በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነበር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ያደሱት፡፡

ሁለቱ ሀገራት የመደበኛ የስልክ አገልግሎትን ካስጀመሩ ከሰባት ዓመታት በኋላ ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ ዳግም ተቋርጧል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የስልክ አገልግሎት ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደተቋረጠ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነሀሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ማቆሙ ይታወሳል፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ያለው አየር መንገዱ በኤርትራ ያለው አሰራር አስቸጋሪ እና ከቁጥጥሩ ውጪ መሆኑ ለበረራው መቋረጥ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *