38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
ስብሰባው “ የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ አፍሪካውያን” በሚል የአፍሪካ ሕብረት ባዘጋጀው የ2025 መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።
በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የሀገራት መሪዎች እና ሌሎች ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁት ቀናት የሚመክረው የመሪዎች ጉባዔ ከሁለት ቀናት በፊት በተጠናቀቀው 46ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል።
ከዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔ አጀንዳዎች መካከል የሕብረቱ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የማካካሻ ፍትህ፣ የአፍሪካ በመንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ጉዳይ እና አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ይገኙበታል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አፈጻጸምና አህጉራዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር፣ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫም የጉባዔው አካል የሆኑ ቁልፍ አጀንዳዎች ናቸው።
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት በአባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከዚህ በፊቱ በተሻለ ቁጥር ያላቸው መሪዎች የተገኙበት ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ቲኑቡ፣ የዛምቢያ፣ ቦትስዋና፣ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎችም ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል፡፡