በኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የቁርአን እና አዛን ውድድር ጥር 25 እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርኣንና የአዛን ውድድር ሽልማት 2ኛ ዙር 2025 ውድድርን ምክንያት በማድረግ በርካታ ሀገራት እንግዶችና ቱሪስቶች በውድድሩ ላይ ለመታደም እንደሚመጡ የዘይድ እብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኑረዲን ቃሲም ተናግረዋል።
የፊታችን ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ከ 60 ሀገራት 100 ተወዳዳሪዎች እንዲሁም 11 ዳኞች ከሁሉም አህጉር ኢትዮጵያ የሚገቡ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የክብር እንግዶች የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ዳግም እንደሚገኙ ተገለጿል፡፡
ይህ መድረክ ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሣብ ቀላል የማይባል ሚና ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የቱሪዝም ሚኒስትር፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከቱሪዝም አንፃር የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት እንግዶችን ለማስጎብኘት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው እየጠበቁ ይገኛል ተብሏል።
የዚህ ዝግጅት ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ አብዛኛው የፋይናስ ምንጭም ከባለቤቱ እንደመሆኑ መጠን ለዚህ አጋዥ አማራጭ የመግቢያ ትኬቶች የማህበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ በአዋሽ ባንክ፤በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ በሂጅራ ባንክ፣ በዳሽን ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎች እና በቴሌብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡
ጥር 25 ቀን 2017 እሁድ እለት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ እስላማዊ ስርኣትን በጠበቀ መልኩ የፀጥታ አካላት የሚስጡትን ትእዛዝ በማክበርና በመጠበቅ እለቱን በደስታ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ የእንግዳ አክባሪነታችንን ባህል በማሳየት አርአያ መሆን ይጠበቅብናል ሲሉ ዶክተር ኑረዲን ቃሲም አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ ክልሎች ሲደረግ የቆያው ማጣሪያ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ከሁሉም ክልል አሸናፊዎች ከየክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቶች ተወክለው በተደረገው የመጨረሻ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወከሉ በ30 ጃዝእ ከወንዶች የሶማሌ ክልል ተወዳዳሪ አንደኛ የወጣ ሲሆን፣በሴቶችና በአዛን ውድድር አዲስ አበባ ከተማን ወክሎ የተወዳደረው አሸናፊ ሆነዋል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ተለይተው፤ለአለም አቀፉ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የቁርዓን ውድድር ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመሪያው ሳይሆን ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ውድድሮች በኢትዮጵያ እና በሌሎች ሀገራት ተካሂደዋል፡፡