የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ተገልጿል፡፡
ከ14 ዓመት በፊት ለግንባታው መሰረት ድንጋይ ሲጣል 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ ግንባታው 97.6 በመቶ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ እንደቀሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተናግሯል፡፡
ህዝቡ እስካሁን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ለግእቡ ግንባታ በበጎ ፈቃደኝነት ያዋጣ ሲሆን በዚህ ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዚህ አካል የሆነና ባንኮችን፣ ኢንሹራንስ ተቋማትንና የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ባሳለፍነው ዓርብ አካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ 110 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታሰበ ቢሆንም በወቅቱ ከተቋማቱ መሰብሰብ የተቻለው 25.9 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡
በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ከአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴው ግድብ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተመረተ ያለው ኤሌትሪክ ኃይል በ2 ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚያመርተው ኤሌክትሪክ ኃይል 5ሺ 150 ሜጋ ዋት ይደርሳል፡፡
አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዉብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።
በሀይል ማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው የሕዳሴው ግድብ በአጠቃላይ ሀይል የሚያመነጩ ሰባት ዩኒቶች ይኖሩታል ተብሏል።
ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በአባይ (ናይል) ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን ግድብ የግድቡ ግንባታ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እየተቃወሙ ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት የተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡
ግብጽ ለሶስትዮሽ ድርደሩ ኢትዮጵያን ተጠያቂ ስታደርግ ኢትዮጵያ በበኩሏ ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ውሎች እንዲቀጥሉ ስለምትፈልግ እንዳልተሳካ አሳውቃለች፡፡