ጾታዊ ጥቃት በሰዎች ላይ አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ችግሮችን የሚያስከትልና ጾታን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም የኃይል ድርጊት ነው፡፡
ፍቅርተ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ስትሆን በምትኖርበት ከተማ ውስጥ የጾታዊ ጥቃት ምን እንደሚመስል ለጠየቅናት ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥታናለች፡፡ “ጾታዊ ጥቃት በቅርብ ሰው፣ በምናውቀው ሰው ነው የሚፈጸመው፡፡ በከተማዋ እና አቅራቢያ ብዙ አይነት ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዳሉ ይሰማኛል” ብላለች፡፡ “ወደ አደባባይ ያልወጡ ብዙ የጾታ ጥቃት ወንጀሎች አሉ” የምትለው ፍቅርተ “በቅርቡ የ14 ዓመት ጓደኛዬ በአጎቷ ተደፍራለች፡፡ እናት እና አባቷ ለማህበራዊ ጉዳይ ከቤታቸው ሲሄዱ አጎቷ ጋር እንድትሆን ብለው በአደራ አስቀመጧት፡፡ ነገር ግን የተሻለ ደህንነት አለው ብለው ባስቀመጧት ቤት ያስቀመጧት ይህች የ14 ዓመት ታዳጊ አጎቷ አስገድዶ ደፍሯታል፡፡ ጉዳዩን ለቤተሰብ ንገሪ ብንላት አያምኑኝም፣ እሱም ለማንም እንዳልናገር አስፈራርቶኛል አለችኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ሰው እስካሁን አልተጠየቀም” ስትልም አክላለች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሴቶች ላይ ጥቃት ያደረሱ ሰዎች በፍርድ ቤት ተቀጡ የሚል ዜና እየሰማን ነው፣ ይህ ጥሩ ነው፣ብዙ ስራ መሰራት ያለበት ግን የተበቁ ወንጀሎችን እንዴት ማውጣት እንችላለን ፣ ህጻናት እና ወጣቶችስ ወንጀሎች ሲፈጸሙባቸው እንዴት ወደ ህግ መሄድ ይችላሉ የሚለው ላይ ነው ብላ እንደምታስብም ፍቅርተ ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ሲዳማ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በሚገባ ሪፖርት እየተደረጉ አይደለም ብሏል፡፡
በኮሚሽኑ የሴቶች ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሀዋርያ ለኢትዮ ነጋሪ እንዳሉት ሲዳማ ክልልን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በቤት ውስጥ እና በቅርብ ሰው ሳይቀር የሚፈጸሙ በመሆናቸው በሚገባ ሪፖርት እየተደረጉ ነው ብለን አናምንም ብለዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ጥቃት በተጨማሪ ለተደራራቢ ጉዳቶች እየተዳረጉ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ዜጎች የጥቃቱ ሚስጥራዊነት በፍትህ አካላት አለመጠበቅ፣ ከለላ አለማግኘት፣ በአመለካከት መዛባት ምክንያት ማሸማቀቅ፣ ማግለል፣ ታሪካቸውን በየቦታው እንዲናገሩ ማድረግ ፣ ለቤተሰብ መፍረስ ፣ መኖሪያ መንደራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ እና ለተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚዳረጉም ጠቅሰዋል፡፡
“በሲዳማ ክልል ጾታዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ወንጀሉን በባህላዊ እና በሽምግልና ለመፍታት መሞከር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ግለሰቦችን ማሸማቀቅ እንዳለ ኢሰመኮ አስተውሏል” ያሉት ርግበ ይህንን ለመፍታትም ፖሊስ እና ሌሎች የፍትህ ተቋማት ባለሙያዎችን ስለ ሰብዓዊ መብቶች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
ከጾታዊ ጥቃት በኋላ የተፈጸሙ ወንጀሎች የፍትህ ሂደት ምን እንደሚመስል ታሪኮችን ለማስተማሪያ እንዲሆኑ እያሰባሰቡ መሆኑን የገለጹት ከሚሽነሯ ይህን መሰረት በማድረግ ለውጥ እንዲመጣ ጥረቶችን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡
ኢሰመኮ ጾታዊ ጥቃቃት ለደረሰባቸው ዜጎች የተቀናጀ ድጋፍ ለማድረግ በሚል የተቋቋመው የሀዋሳ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ማጠናከር፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ የወንጀል መርማሪዎች እና አቃቢ ህጎችን አቅም ማሳደጊያ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በሲዳማ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በቀለ ለግደ በበኩላቸው በክልሉ አሁንም አጠቃላይ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃቶች እየደረሱ ቢሆንም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ግን እየቀነሱ መጥተዋል ብለዋል፡፡

“አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እያገኙ ነው፣ ይህ ወንጀሎቹን እንዲቀንሱ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የጾታዊ ጥቃት ወንጀሎች በየጊዜው እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃቶች ከክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፣ የስርዓተ ጾታ ለውጥ እንዲመጣ ከሀይማኖት እና ሀገር ሽማግሌዎች ጋርም እየሰራን ነው” ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡
ከ2016 ዓ.ም በፊት በነበሩ ዓመታት ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መጠን በየዓመቱ ከ50 በላይ ነበር የሚሉት አቶ በቀለ በተያዘው በጀት ዓመት የዚህ ወንጀል መጠን ወደ ወደ ዘጠኝ ዝቅ ማለቱንም አንስተዋል፡፡
በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ስር በተቋቋመው የአንድ ማዕከል ውስጥ ከፖሊስ፣ ፍትህ እና ጤና የተውጣጣ ቡድን የተቀናጀ የህግ እና ጤና ድጋፍ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ይህ የአንድ ማዕከል ለተጎጂዎች የጤና እና ስነ ልቦና አገልግሎት ከመስጠቱ ባለፈ ወንጀሎች ተደብቀው እንዳይቀሩ እና አጥፊዎች ተገቢው ይህግ ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ከአንድ ሳምንት በፊት የፍርድ ውሳኔ ያገኙት በሦስት ህጻናት ላይ የደረሱ አስገድዶ መድፈር ወንጀል የምርመራ መዝገቦች እና አጥፊዎች እስከ 18 ኣመት እስራት እንደተላለፈባቸው ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ የወንጀል ምርመራ እና የፍርድ ሂደት በአስተማሪነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው የሚሉት አቶ በቀለ አባት የራሱን ልጅ ደፍሮ ከቅጣት ማምለጥ እንደማይችል ትልቀቅ ማሳያ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ በቀለ በምላሻቸውም የተዛባ የስርዓተ ጾታ አመለካከትን ለማስቀረት ረጅም ጊዜ ይፈጃል፡፡ በክልሉ እንደ አስገድዶ መድፈር አይነት ወንጀሎች እየቀነሱ ቢመጡም አመለካከቱ ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልተፈታም ብለዋል፡፡
የግንዛቤ ፈጠራ ስራው በሰፊ በመሰራቱ ምክንያት ከዚህ በፊት ወንጀል ፈጻሚዎች ሳይጠየቁ ይቀር የነበረውን ሂደት አስቀርቷል፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመባቸው እና ቤተሰቦቻቸው በግልጽ ወደ ህግ እየመጡ እና ተጠያቂነት እየሰፈነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“ከዚህ በፊት ወንጀል ሲፈጸም በተለይም ሴቶች ያለ እድሜያቸው ሲዳሩ ዝም ብሎ ማየት እና እድሜን ሳይቀር እየዋሹ ያለ እደሜያቸው እንዲያገቡ ጫና ማድረግ ይደረግ ነበር፣ እንዲሁም ሴቶች ሲጠለፉ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈጸምባቸው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከማድረግ ይልቅ ጉዳዩን በሽምግልና እና በእርቅ ለመፍታት መሞከር ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ የተለመደ እና የተሳሳተ አመለካከት እየተፈታ ነው፡፡ ወንጀል የፈጸመ ሁሉ ይጠየቃል” ሲሉም አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡