በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች እየተደጋገሙ ሲሆን እስካሁን መኖሪያ ቤቶች ላይ የተወሰኑ ጉዳቶችን ከማድረስ የዘለለ ከባድ ጉዳት አላደረሱም፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ ከ30 ጊዜ በላይ በአፋር ክልል አዋሽ ከተማ አቅራቢያ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ከ60 ዓመት በኋላ ከፍተኛ የጠባለ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟል፡፡
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 8 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟል፡፡
በዚህ አደጋ ምክንያት በአፋር ክልል ባሉ መኖሪያ ቤቶች እና የመንግስት ተቋማት ላይ አነስተኛ ጉዳት ያጋጠመ ሲሆን ንዝረቱ አዲ አበባ ድረስ ተሰምቷል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው ማስታወቂያ የርዕደ መሬቱ ማዕከል ከሆኑ 12 ቀበሌዎች 80 ሺህ ዜጎችን ሊፈጠር ከሚችለው አደጋ ለመጠበቅ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዘዋወር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ማዕከላቸውን አድርገው የተለያየ መጠን ያላቸው የርዕደ መሬት ክሥተቶች በተደጋጋሚ መከሠታቸውን ተቋሙ አስታውቋል።
ክሥተቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እያደጉ ይገኛሉ ያለው ተቋሙ በተለይም በዚህ ሳምንት በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ 5.8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ መንቀጥቀጥ መከሠቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
መንግሥት ክሥተቶቹን በዘርፉ ባለሞያዎች በቅርብ እየተከታተለ መሆኑንም አስታውቋል።
በተጨማሪም በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል (epicenter) የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ መንግሥት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቦታው ተሰማርተው የጉዳቱን መጠን አየገመገሙ ናቸውም ተብሏል።
በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማሥፈር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው።
በተጨማሪም ርዕደቱ በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በኢኮኖሚ ተቋማት እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ በመከታተል ላይ እንደሚገኝም መንግስት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የመሬት መንቀጥቀጡ በዋና ዋና ከተሞች የጎላ ተጽዕኖ ያላደረሰ ቢሆንም ዜጎች በባለሞያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩም መንግስት አሳስቧል።