በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች እየተደጋገሙ ሲሆን እስካሁን መኖሪያ ቤቶች ላይ የተወሰኑ ጉዳቶችን ከማድረስ የዘለለ ከባድ ጉዳት አላደረሱም፡፡
አደጋው እያጋጠመ ያለው በአፋር ክልል አዋሽ ልዩ ስሙ ፈንታሌ አካባቢ እንደሆነ የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በአዋሽ ፈንታሌ እየተከሰተ ባለዉ ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት ምክንያት ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እየለቀቁ ሲሆን እስካሁን ከ2,500 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ በተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች እስካሁን ከፍተኛው 5 በሬክተር ስኬል 5 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ነው።
በአደጋው ከ100 በላይ ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸዉ ሲሆን፤ 2 ሺሕ 560 ሰዎች መፈናቀላቸውን እና እንሰሳት መሞታቸውን የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር አቶ አደም ባሂ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም በቀን ውስጥ እስከ 10 እና ከዛ በላይ እየተከሰተ አስጊነቱም እየጨመረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታ ውስጥ ብቻ ከ14 ጊዜ በላይ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከፍተኛው 4.8 ሬክተር ስኬል ነበር።
በኢትዮጵያ ሁኔታ የስምጥ ሸለቆ በሚባሉ አካባቢዎች ያሉ ቦታዎች ለመሬት መንቀጥቀጥ የበለጠ ተጋለጭ ናቸው፡፡
ከዚህ አንጻር ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚባለው ከቀይ ባህር ተነስቶ መቀሌ፣ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ አንኮበር፣ ደብረብርሃን፣ አዋሽ፣ አዳማ፣ መተሃራ ፣ፈንታሌ፣ መቂ፣ ዝዋይ፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ አዲስ አበባ (አቃቂ ቃሊቲ እና አካባቢው) ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ በ1898 ዓ.ም ላይ የተከሰተ ሲሆን አደጋው ያጋጠመው ላንጋኖ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ ነበር፡፡
ይህ አደጋ 6 ነጥብ 8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ ሲሆን በወቅቱ በአዲስ አበባ የነበሩ ቤተ ክርስቲያናትን አፈራርሶ ነበር፡፡
ሁለተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ያጋጠመው ደግሞ በ1953 ዓ.ም ሲሆን ከአዲስ አበባ-ደሴ ባለው ዋና መስመር ላይ ልዩ ስሙ ካራቆሬ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ አጋጥሞ እንደነበር የከርሰ ምድር ተመራማሪው ዶክተር መሰለ ሀይሌ ተናግረዋል፡፡
ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ 6.75 ሬክተር ስኬል ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ ቦታዎችን በተለይም ማጀቴ፣ ኮምቦልቻ- ደሴ እና የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የነበሩ መኖሪያ ቤቶችን እንዲፈርሱ ምክንያት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ሶስተኛው አደጋ ደግሞ በ1960 ዓ.ም ሰርዶ ተብሎ በሚጠራው የአፋር ማህበረሰብ በሚኖርበት ቦታ ሰመራ አካባቢ 6.4 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ አደጋ አጋጥሞ ቤቶችን አውድሞ አልፏል ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እስከ 6 ነጥብ 8 ሬክተር ስኬል የተመዘገቡ ከ30-40 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ያጋጠማት ሲሆን ብዙዎቹ የከፋ አደጋ ያላደረሱት ከተሞች ስላልተስፋፉ እና ረጃጅም ህንጻዎች ስላልነበሩ መሆኑን ዶክተር መሰለ ተናግረዋል፡፡