የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አባል ማህበራት የሰራተኞች ጥያቄ ካልተመለሱ ስራ የማቆም አድማና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንገደዳለን ሲል አስጠንቅቋል፡፡
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በመንግስት እንዲወሰንና ከደመወዝ ላይ የሚቆረጠው ከፍተኛ_ግብር እንዲቀንስ መንግስት በተደጋጋሚ ቢጠየቅም እስካሁን ምላሽ አልሰጠም ተብሏል፡፡
በመሆኑም ከዚህ በኋላ ሰራተኞች ወደ ስራ ማቆም አድማና ወደ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያመሩ እንደሚችሉ ማህበራቱ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን የኢትዮጵያን ሰራተኞች ይወክላሉ ከሚባሉት አባላቱ ጋር ባሳለፍነው ሳምንት አድርጎት በነበረው ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ አባላቱ በሰራተኞች ጥቅም ዙሪያ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ማህበራቱ በመግለጫቸው እስካሁን ስናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎቻችን በመንግስት ባለመመለሳቸው ከዚህ በኋላ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ እንገደዳለን ማለታቸውን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን የውጭና ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ አያሌው አህመድ ለሸገር ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ_ሰራተኞች ወኪል ተደርገው የሚታዩት እነዚህ የኮንፌደሬሽኑ አባላት በአቋም መግለጫቸው ያሰፈሩት ወደ ተግባር ከማስገባታቸው በፊት ኮንፌደሬሽኑ ምን ለማድረግ አስቧል? ላልናቸው አቶ አያሌው ሲመልሱ፤ ሰራተኞቹ ወደዚህ ተግባር ከመግባታቸው በፊት የኮንፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከመንግስት ምላሽ ለማግኘት የራሱን ጥረት ያደርጋል ብለውናል፡፡
በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደሩ ሰራተኞች አሁን ያለውን የኑሮ ጫና መቋቋም እንዲችሉ የሚከፍሉት ግብር እንዲቀነስ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩን በደብዳቤ በድጋሚ መጠየቃቸውን ያስታወሱት ኃላፊው ደብዳቤው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረስ አለመድረሱን የምናረጋግጥ ይሆናል፤ ምላሻቸውንም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ በኮንፌደሬሽኑ መንግስትን በተለያዩ ደረጃዎች በድጋሚ በመጠየቅ ምላሽ የሚያገኝ ከሆነ በጉባኤው የተቀመጠውን ማድረግ ማለትም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግም ይሁን የስራ ማቆም አድማ ማድረግ ሳያስፈልግ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ሀላፊው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሰራተኞችን መብት ለማስከበር በሚል የተቋቋመ ሲሆን በስሩም ከ2 ሺህ 300 በላይ ተቋማትን የያዘ ነው፡፡