ፕሬዚዳንት ማክሮን ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው ተባለ

ፕሬዝዳንት ማክሮን በአዲስ አበባ ቆይታቸው በእድሳት ላይ ያለውን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ይመርቃሉ ተብሏል

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ቀንድ ይመለሳሉ ተብሏል፡፡

ፕሬዝዳንቱ የፊታችን ሐሙስ ማለትም ታህሳስ 11 ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ጉብኝት እንደሚያርጉ አፍሪካን ኢንተለጀንስ ዘግቧል።

በዚህ ጉብኝት ፕሬዝዳንት ማክሮን አዲስ የታደሰውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መንግስትን ይመርቃሉ ተብሏል፡፡

ብሔራዊ ቤተ መንግስት ላለፉት 18 ወራት ሰፊ እድሳት የተደረገለት ሲሆን ከሚቀጥለው ሳምንት በኋላ ለጎብኚዎች ክፍት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ቤተ መንግሥቱ ከ1955 ጀምሮ ዓ.ም የአፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግስት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ላለፉት ዓመታት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ይፋዊ መኖሪያ ሆኖ እና የመንግሥት ሥራ የሚካሄድበት ቦታ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። 

ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠገኑ የገንዘብ እና እውቀት ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሲሆን የብሄራዊ ቤተ መንግስትን ጨምሮ የላሊበላ ውቅር አብተ ክርስቲያናት እና ሌሎችንም ቅርሶች እድሳት ድጋፍ አድርጋለች፡፡

ፕሬዚደንት ማክሮን እኤአ በ2019 አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት የቅርስ እድሳትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ስምምነቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል።

ከቅርስ እድሳት በተጨማሪም ፈረንሳይ የኢትዮጵያ የባህር ሀይልን እንደ አዲስ ለማደራጀት እና ሌሎች ወታደራዊ ስምምነት ነበራት፡፡

ይህ የባህር ሀይልን ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ፈረንሳይ ከዚህን ስምምነት መውጣቷን በወቅቱ አስታውቃ ነበር፡፡

ጦርነቱን ያስቆመ ስምምነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ መፈረሙን ተከትሎ ፈረንሳይ ወደ ስምምነቱ ስለመመለሷ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም፡፡

ይህ የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት ኢትዮጵያ የባህር ሃይል አባላትን ስልጠና መስጠት፣ የጦር መሳሪያ ግዢ እና ሌሎች ወታደራዊ ትብብሮችን ማድረግን ያካተተ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፉት ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ ፓሪስ አምርተው ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር መክረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *