በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የአንበሳ እና የስጋ በል እንስሳት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ካህሳይ ገብረ-ተንሳይ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉት አንበሶች ቁጥር ከ1 ሺ እንደማይበልጥ ተናግረዋል።
በሃገሪቱ አሁን ላይ አንበሶች ያሉበት ሁኔታ ለማወቅ ጥናት ማድረጋቸውን የገለፁልን ተመራማሪው በአዋሽ እና በመካከለኛው አዋሽ በተደረገው ጥናት መሰረት ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም ግን ሁሉም ርብርብ ካላደረገ አንበሶቹን ልናጣ እንችላለን ብለዋል፡፡
ተመራማሪው እንደሚሉትም ህገወጥ የነዋሪዎች ሰፈራ፣ የደን ጭፍጨፋ መኖር፣ የእርሻ ስራ እና ግጦሽ መበራከት አንበሶቹ የሚፈልጉትን ምግብ እንዳያገኙና በምግብ ሰንሰለት ውስጥ ችግር እንዲፈጠር ብሎም ለህገወጥ አደን በስፋት ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የባህል መድኃኒት ቀማሚዎች ፊታቸውን ወደ አንበሳ አጥንት ማዞራቸው እንስሳቶቹን ለህገወጥ አደን ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑና ቁጥራቸው እንዲመናመን ማድረጉን በባለስልጣኑ ተመራማሪው ይናገራሉ።
ቀጣይነት ያለው ጥናት በመላ ሃገሪቱ ለማድረግ ማቀዳቸውን የገለጹልን ተመራማሪው የሁሉም ባለድርሻ አካላትን እገዛ ጠይቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር በባህልም ይሁን በሌላ ሰፊ ቁርኝት እንዳለው የሚነገረው አንበሳ ከመንግስትም ይሁን ከማህበረሰቡ ከፍተኛ ትኩረት ካልተደረገለት የአንበሳ ስሙ ብቻ ሊቀር እንደሚችል እና አንበሳ የሚባል ነገር ታሪክ ሊሆን ይችላል ሲሉም አሳስበዋል
ኢትዮጵያም የዱር እንስሳትን ለህጋዊ አደን ከሚያዘጋጁ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ለዚህ የሚረዳ አሰራር መዘርጋቷን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ወርቁ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአራት ክልሎች ሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን በማካሄድ ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ክምላው ዓለም ለሚመጡ ጎብኚዎች ሕጋዊ የዱር እንስሳት አደን እየተካሄደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለሕጋዊ አደን የተፈቀዱ እና ያልተፈቀዱ የዱር እንስሳት ያሏት ሲሆን አንበሳ፣ ነብር፣ የደጋ አጋዘንን ጨምሮ በአጠቃላይ 54 የዱር እንስሳት ለአደን ተፈቅደዋል፡፡
እንዲሁም ዋልያ፣ ዝሆን፣ ተኩላ፣ አውልድጌሳን ጨምሮ 48 የዱር እንስሳት ደግሞ ለአደን ከተከለከሉት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን የዱር እንስሳት ለማደን ዝቅተኛው 50 ዶላር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ክፍያን እንደምታስከፍል አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
የመጥፋት አደጋ ተደቅኖበታል የተባለው አንበሳን ለማደን 4 ሺህ 500 ዶላር መክፈል እንደ ግዴታም አስቀምጣለች፡፡