ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለነበራት ወዳጅነት መበላሸት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ተጠያቂ አደረገች

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት የተበላሸው በጠቅላይ ሚኒስር አብይ አህመድ አማካኝነት ነው ብላለች፡፡

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ዮሃንስ ተክለሚካኤል ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ይህንን የተናገሩት ባልተለመደ ሁኔታ በብሪታኒያ የኤርትራ ኤምባሲ የዩቲዩብ ቻናል ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሲሆን፤ ቪዲዮው ይፋ ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ እንዲነሳ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ተሻሽሎ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፤ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም የአገራቱ ግንኙነት ተቀዛቅዟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እና የስልክ ግንኙነት መቋረጥ ግንኙነቱ ስለመሻከሩ ማሳያ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ቆይቷል።

በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር ዮሃንስ ተክለሚካኤል ‘ኤርትራ ኤምባሲ ሚዲያ’ (Eritrea EmbassyMedia) ከተሰኘ የዩቱዩብ ቻናል ጋር ባደረጉት ያልተለመደ ቃለ መጠይቅ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት “እንደ ቀድሞው አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መበላሸት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ተጠያቂ አድርገዋል።

“በአሁኑ ወቅት አራት ኪሎ የሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚፈጥራቸው ችግሮች በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ሞቶ እንዲቀበር አድርጓል” በማለት ያለው ግንኙነት ችግር እንደገጠመው አመልክተዋል።

አምባሳደር ዮሃንስ ተክለሚካኤል የሰጡት ቃለ ምልልስ በአሁኑ ጊዜ ከዩቲዩብ ቻናሉ ላይ የተነሳ ሲሆን፤ ልምን እንደተነሳ ምክንያቱም አልተገጸም።

በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነበር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ያደሱት፡፡

ሁለቱ ሀገራት የመደበኛ የስልክ አገልግሎትን ካስጀመሩ ከሰባት ዓመታት በኋላ ዳግም ተቋርጧል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የስልክ አገልግሎት ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደተቋረጠ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሳምንታዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ዙሪያ መግለጫ በሰጡት ወቅት ስለ ጉዳዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

አምባሳደር ነቢያት በምላሻቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ምንም የተቀየረ ነገር እንደሌላ እና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነሀሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ማቆሙ ይታወሳል፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ያለው አየር መንገዱ በኤርትራ ያለው አሰራር አስቸጋሪ እና ከቁጥጥሩ ውጪ መሆኑ ለበረራው መቋረጥ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *