የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን በሰብአዊ መብት ሥራዎች ታዋቂ የሆኑ ድርጅቶችን እንዳሸገ ተገልጿል፡፡
ከታገዱት ድርጅቶች መካከልም “የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል” (CARD) እና “ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ” (AHRE) ይገኙበታል።
ባለሥልጣኑ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እና በዚህ ሳምንት ለድርጅቶቹ በተናጠል በላከው ደብዳቤ፣ ድርጅቶቹ ከማንኛውም እንቅስቃሴ መታገዳቸውን አስታውቋል ሲል ዋዜማ ሬዲዮ ዘግቧል።
ለእገዳው የሰጠው ምክንያት “ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባው ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርና የህዝብ ጥቅምን የሚጎዱ ተግባራት ላይ በመሰማራቱ ከባድ የህግ ጥሰት መፈጸሙን ማረጋገጥ ተችሏል” የሚል ነው።
ከሁለቱ የሰብዓዊ ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎችም እንደታገዱ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህ እርምጃ መንግሥት በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በሚሠሩ ድርጅቶች ላይ ሲያደረግ የቆየው ጫና የመጨረሻ ከፍታ ነው ሲሉ ስለጉዳዩ በቅርብ የሚያውቁ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
የእግድ እርምጃው በድርጅቶቹ መሪዎች አካባቢ የተጠበቀ እንዳልነበር ለመረዳት ችለናል። የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን መያዶችን የማገድ ስልጣን ቢኖረውም “የአሁኑ እርምጃ በሕጉ የተዘረዘረውን ቅደም ተከተልና ቅድመ ሁኔታ የሚጥስ ነው” ብለዋል ሌላ የሕግ ባለሞያ።
ድርጅቶቹ እግዱን በሕግ የመቃወም መብት ይኖራቸዋል የተባለ ሲሆን ለባለሥልጣኑ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እገዳው የተላለፈበት ሂደት እንዳልሆነ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እኛ የማንከፍላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ደመወዝ ለሚከፍሏቸው ሪፖርቶቻቸውን እየላኩ ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እንዲያከብድር እና እንዲያስከብር በተደጋጋሚ በሚያወጡት መግለጫ አሳስበዋል፡፡
ባሳለፍነው ነሀሴ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሰብዓዊ ድርጅት ሰራተኞች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አልቻሉም በሚል መግለጹ ይታወሳል፡፡
ምክር ቤቱ በመግለጫው በተለይም በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን ለመድረስ ሲጓዙ ግድያ፣ እገታ እና ሌሎች እንግልቶች እንደሚደርሰባቸው አስታውቋል፡፡
ከ2019 እስከ ሚያዝያ 2023 ድረስ ባሉት ጊዜ ውስጥ 36 የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሰራተኞች እንደተገደሉ ሲገለጽ ተቋማቱ በእቅዳቸው መሰረት ያለሙትን ስራ ተንቀሳቅሰው መስራት እንዳልቻሉ በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡