የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማደጉ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ከባንኮች የውጭ ንግድ ግብይት ብቻ በየወሩ 500 ሚሊዮን ዶላር እያገኘች እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ካሳለፍነው ሐምሌ ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲመራ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምኅረቱ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከወጪ ንግድ ብቻ በወር በአማካይ 500 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል ብለዋል፡፡

ዋና ገዢው አክለውም የባንክ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወደ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ማደጉንም ገልጸዋል፡፡

አቶ ማሞ አክለውም ከኹለት ሳምንት በፊት በባንኮች መካከል በተጀመረው የእርስ በርስ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግብይት እንደተካሄደም ተናግረዋል።

የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ ነጋዴዎች ካገኙት የውጭ ምንዛሬ ገቢ ላይ 50 በመቶውን ላልተወሰነ ጊዜ አገር ውስጥ በሚገኝ የባንክ ሒሳባቸው ማስቀመጥ የሚችሉበት አሠራር ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ዋና ገዢው አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ንግድን ለማበረታታት በሚል ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ግብይትን በገበያ እንዲመራ ውሳኔ ያስተላለፈች ሲሆን የብር የመግዛት አቅም ከእጥፍ በላይ ቀንሷል፡፡

አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአማካኝ በ120 ብር እየተመነዘረ ሲሆን በጥቁር ገበያ ደግሞ እስከ 140 ብር ድረስ እየተመነዘረ ይገኛል፡፡

ከአንድ ወር በፊት ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ በላይ መሆን እንደሌለበት ብሄራዊ ባንክ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ገልጸዋል።

ከተገኙ ገቢዎች መካከልም ለጎረቤት ሀገራት ከተላከ የኤሌክትሪክ ሽያጭ፣ከቡና ንግድ፣ ማዕድናት፣ከቢትኮይን ግብይት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ ከቢትኮይን ግብይት 27 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን በአጠቃላይ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ 55 ሚሊዮን ዶላር ከቢትኮይን ግብይት ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ፓወር (EEP) አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *