ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናባዊ ገንዘብ ወይም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ፍላጎት እየጨመረ ሲሆን በኢትዮጵያም አጀንዳ ከሆነ አምስት ዓመት ሆኖታል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትኛውንም ክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት እንዳልፈቀደ እና ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ሰዎችም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቆ ነበር፡፡
ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የቢትኮይን ግብይት መፈጸም የሚያስችሉ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርጉ ኩባያዎች ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት እንዲደረግ ያልፈቀደች ሲሆን የዳታ ማዕከል ግንባታዎች እንዲካሄዱ ግን ስምምነቶችን በመፈራረም ላይ ነች፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የዎልስትሪቱ ቢትፉፉ የተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚያስችለውን ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ማካሄድ የሚያስችል የ80 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ሀይል መሰረት ልማት መግዛቱን ገልጿል፡፡
ቢትፉፉ የተሰኘው ይህ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኤሌክትሪክ ዋጋ ርካሽ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ለኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ የሚያወጣው ወጪ በ175 በመቶ እንደጨመረበት የገለጸ ሲሆን ይህም የትርፉን 75 በመቶ ለሀይል እንዲያወጣ ዳርጎታል ተብሏል፡፡
ከሰባት ወራት በፊት ዌስት ዳታ ማዕከል የተሰኘው ኩባንያ የ250 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የቢትኮይን ግብይት እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ እና ቻይና ክሪፕቶከረንሲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከላቸውን ለመክፈት ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የዳታ ማዕከላትን ለመገንባት ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ናቸው፡፡
ራክሲዎ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የዳታ ማዕከል ድርጅት በአዲስ አበባ በሚገኘው አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ገንብቶ ማጠናቀቁን ከአንድ ዓመት በፊት አስታውቋል፡፡
የክሊፕቶከረንሲ ፍላጎት እየጨመረ የመጣ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን ከ69 ሺህ ዶላር በላይ በመመንዘር ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ለክሪፕቶከረንሲ ግብይት ትኩረት እንደሚሰጡ ከተናገሩ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ እየጨመረ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሀገሯ እንዲመጡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ሌሎች ተቋማት በኩል እያስተዋወቀች ትገኛለች።
በዚህም መሰረት እስካሁን 25 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር የሀይል አቅርቦት ስምምነት በመፈራረም ላይ ናቸው።
ከ25ቱ ተቋማት ውስጥም አራቱ ሥራ መጀመራቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የገበያና ቢዝነስ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ህይወት እሸቱ እንዳስታወቁት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎቹ በሀገር ውስጥ ኃይል የሚጠቀሙ ቢሆንም የፍጆታ ሂሳባቸውን በዶላር እንዲከፍሉ ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ፍቃድና ሌሎች አስፈላጊ መስፈርቶችን ካሟሉት ከሃያ አምስቱ ድርጅቶች መካከል አራቱ ከ10 እስከ 100 ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል መጠቀም ጀምረዋልም ተብሏል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ከተከናወነው ሽያጭ አስቀድመው ሥራ ከጀመሩት ከሁለቱ የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ብቻ ከሁለት ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።