ኦብነግ ከሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳትፎ ራሱን አገለለ

የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ከሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳትፎ እራሱን ማግለሉን አስታወቀ

 የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ድርጅት አሳታፊነትና ግልጸኝነት ስላላየሁበት ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳታፊነት እራሴን አግልያለሁ ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በሱማሌ ክልል የገዢው ፓርቲ መዋቅር ተሳታፊዎችን የሚለይበትና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ድምጽ የሚያፍንበት ህገ-ወጥ  አሰራር መዘርጋቱን የሚገልጸው ፓርቲው በዚህ ሂደት ውስጥ በምክክር መሳተፍ ረብ የለሽ ነው ሲልም ገልጿል፡፡

ይህ አግላይ አሰራር አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትን አላማ የሚጥስ ነው ሲልም በምክክር ኮሚሽኑ ሂደት ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡

ፓርቲው ከሱማሌ ክልል ውጪ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳሱ የታጠቁ ሃይሎች ባልተሳተፉበት ሁኔታ እንዴት የምክክር ሂደቱ ሊሳካ ይችላል ሲልም በጥያቄ መልስ አንስቷል፡፡

በቀጣይም ሁሉን አቀፍ የድርድር መድረክ እስካልተዘጋጀ ድረስ በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንደማይችልም ጠቁሟል፡፡

ኦብነግ ለሶማሊ ነጻነት የሚታገል ድርጅት ሲሆን ለዓመታት በስደት ከነበረበት በ2010 ዓ.ም ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ለማድረግ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ስምምነት አድርጎ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ አይዘነጋም፡፡

ከኦብነግ በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮነንግረስ እና ሌሎችም ፓርቲዎች ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር አብረው እንደማይሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እና የምክክር መድረኮችን ለማመቻቸት በሚል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

ኮሚሽኑ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመዘዋወር ለአለመግባባት ምክንት ናቸው ያላቸውን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ባሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ምክንያት በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች አካባቢዎች ጦርነት እና ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን ተፋላሚ ወገኖች በሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካኝነት ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን አለመተማመን በመኖሩ አልተሳካም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *