ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች

በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የ10 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በኮሪያ ሪፐብሊክ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ መካከል የኢትዮጵያ የጥራት አመራር አቅም ማጎልበቻ ፐሮጀክት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የግብርና እና የተቀናበሩ የግብርና ምርት ውጤቶች ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ላይ ያተኩራል የተባለ ሲሆን ለዚህም ደቡብ ኮሪያ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ታደርጋለች ተብሏል፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ በኢትዮጵያ የኮሪያ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሚስተር ሃን ዲዩግ ቾ እንደገለፁት የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት ታረካዊ ነው ያሉ ሲሆን በኮሪያ ጦርነት ወቅት ከ6000 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ህዝብ ተዋግተው የደም ዋጋ የከፈሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክት ስምምነቱ የኮሪያ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነትን እንደሚያጠናክር፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ የገለፁት ሚስተር ሓን ይህ ፕሮጀክት ኮሪያ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር  ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የፕሮጀክት ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፉ የሁለቱን አገራት አጋርነትና ትብብር ከማጠናክር ባለፈ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገታችን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የጥራት መሰረተ ልማት እንደሚያጠናክርና የግብርናውን ዘርፍና የተቀናበሩ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ እና የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ የ10 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነትን በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወሳል።

የገንዘብ ድጋፉ የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን ይውላል የተባለ ሲሆን በተለይም የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል።

የወተት ምርታማነትን የሚያሳድገው ይህ ፕሮጀክት በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት እንደሚተገበር የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጾ ነበር።

ፕሮጄክቱ በወተት ልማት እና እንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን መደገፍ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ተገልጿል።

የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ፣ የወተት ምርታማነትን መጨመር፣ በማህበር የተደራጁ ወተት አቅራቢዎችን የገበያ እድሎችን ማስፋት፣ ተጨማሪ ሌሎች አሰራሮችን መዘርጋት የፕሮጀክቱ ዓላማ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ የሚባል ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ በሴኡል ጉብኝት አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚተገበሩ የ1 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈራረማቸውም አይዘነጋም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *