በኢትዮጵያ ከሞቱ ሰዎች ኩላሊት እንዲለገስ የሚፈቅድ ህግ እንዲዘጋጅ ተጠየቀ

ኩላሊት ከሞተ ሰው እንዲወሰድ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ከስድስት ዓመት በፊት የተዘጋጀ ቢሆንም እስካሁን መልስ እንዳላገኘ የኩላሊት ህመምተኞች ማህበር ተናግሯል፡፡

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ የኩላሊት ልገሳን ከቤተሰብ ውጭ እንዲለገስ የማይፈቅደው የኢትዮጵያ የጤና ህግ  እንዲሻሻል ቢጠየቅም መልስ አለማግኘቱ ችግር እንደሆነ ተነግሯል።

በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት የጤና ህጎች ረቂቅ አዋጅ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን ስለ ኩላሊት ልገሳ የሚያወራው ህግ ግን እስካሁን እንዳልቀረበ  በኩላሊት ተካሚዎች ማህበር በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ኩላሊት ከሞተ ሰው በቀዶ ህክምና ከበጎ ፈቃደኞች እንዲወሰድ የሚረዳ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ላለፉት ስድስት ዓመታት እየተጠየቀ ቢቀጠልም እስካሁን ተግባራዊ መሆን እንዳልተቻለም  አስታውቀዋል።

ከቤተሰብ የሚደረገው የልገሳ ሂደትም በለጋሽ በኩል በሚያጋጥሙ ህመሞች እና ከለጋሽ በጎ ፈቃደኞች ጋር ባለመመሳሰል ምክንያት የንቅለ ተከላ አለመሳካቶች ይስተዋላሉ።

በተደጋጋሚ ለተወካዮች ምክር ቤት ረቂቁ ይቀርባል የሚል መልስ እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት አቶ ሰለሞን እስካሁን ግን ጠብ ያለ ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የአይን ብሌን ልገሳ ሰዎች በህይወት እያሉ ወደውና ፈቅደው በሚፈርሙት መሰረት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ልገሳ ማካሄድ እየተሰራበት እንደሚገኝ አንስተው ለኩላሊትም ተመሳሳዩን መደረግ ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ በመሰጠት ላይ የነበረ ሲሆን ኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ማዕከሉ ስራ ካቆመ በኋላ መቀጠል አልቻለም፡፡

ዶ/ር ሞሚና አህመድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያደረገች ሐኪም ስትሆን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 17 የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላን በበላይነት መርታለች፡፡

ይህ የንቅለ ተከላ ህክምና ማዕከል በአጠቃላይ ለ102 ኢትዮጵያዊን ህሙማን የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማከናወኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህክመናው ከተቋረጠ በኋላ በባለሙያዎች መልቀቅ ምክንያት ማዕከሉ እስካሁን ዳግም ስራ መጀመር አልቻለም፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ወርቁ ባንድ ወቅት ከሚዲያዎች ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የኩላሊት ህመምተኛ ኩላሊት የሚለግሰው ዘመድ ከሆነ ሰው ብቻ መሆኑን እና ይህም የሚደረገው በዋናነት ህገወጥ የአካል ሽያጭን ለመከላከል እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስካሁን በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቷል ስለተባለው ሕግ ያልተናገረ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ዜጎች የዘር ፍሬ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲለግሱ እና በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ መውለድ ላልቻሉ ባለትዳሮች ህክምና ማግኘት እንዲችሉ የሚፈቅድ ህግ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *