የአራዳ መጠጥ ምርቶች አቅራቢ የሆነው ኮማሪ ቤቭሬጅ ለሃይኒከን መሸጡ ተገልጿል፡፡
በአጭር ጊዜ በተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የአራዳ መጠጦች አምራች ኮማሪ ፋብሪካውን ለሃይኒከን ለመሸጥ ሲያደርግ የነበረው ድርድር ከሳምንት በፊት አጠናቋል ተብሏል፡፡
የሽያጩ ድርድር ለበርካታ ወራት ሲደረግ ነበር የተባለ ሲሆን ሁለቱ ወገኖች በሀምሌ ወር ወደ መጨረሻ የድርድር ምእራፍ ቢሸጋገሩም ሀምሌ 22 ቀን 2016 ዓም ወደ ትግበራ የገባውን የምንዛሬ ገበያ ለውጥ ተከትሎ ድርድሩ በድጋሚ ሲደረግ እንደነበር ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የሽያጩ ዋጋ በዚህ ወር መጨረሻ በይፋ ይገለጻል የተባለ ሲሆን ሁለቱ ወገኖች በዚሁ ወቅት በይፋ ፋብሪካውን እንደሚረካከቡ ተገልጿል፡፡
ኮማሪ ከአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ 96 ኪሜ ርቀት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጨኬ አካባቢ በገነባው ፋብሪካ በሰዐት 27 ሺ ጠርሙስ አራዳ ቢራን ጨምሮ የተለያዩ አልኮል እና ከአልኮል ነጻ የሆኑ ምርቶችን ያመርታል፡፡
ከሶስት አመት በፊት ወደስራ የገባው እና በኢትዮጵያ ባለሃብቶች የተቋቋመው ፋብሪካው ከ29 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ነው፡፡
ሃይኒከን ኩባንያ እኤአ በ2011 ሀረር እና በደሌ ቢራ ፋብሪካዎችን ከመንግስት በ163 ሚሊየን ዶላር በመግዛት ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጠጥ ገበያ የተቀላቀለው፡፡
በአለም ታዋቂ የሆነው የቢራ አምራቹ ሀይኒከን ኩባንያ እኤአ በአዲስ አበባ 2015 ቂሊንጦ ላይ በ310 ሚሊየን ዩሮ ባስገነባው ዘመናዊ የቢራ መጥመቂያ ታዋቂውን አለም አቀፍ ብራንዱን ጨምሮ የተለያዩ የቢራ ምርቶችን እያመረተ በማምረት ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ 12 የቢራ ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን ሀይኒከን ኩባንያ ዋሊያ፣ ሀረር፣ በደሌ እና ሀይኒከን ቢራዎች በማምረት በኢትዮጵያ ትልቁ የቢራ ፋብሪካ ነው፡፡
ከ102 ዓመት በፊት የተቋቋመው ቅዱ ጊዮርጊስ ቢራ በኢትዮጵያ ቢራ ታሪክ የመጀመሪያው ፋብሪካ ሲሆን ሜታ፣ ዘቢዳር እና ራያ የተሰኙ ብራንድ ቢራዎችን በማምረት ላይ ነው፡፡