ላለፉት ዘጠኝ ወራት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ታዬ የኢትዮጵያ ስድስተኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
ሁለቱ ምር ቤቶች በጋራ ባካሄዱት የመክፈቻ ስነ ስርዓትም አምባሳደር ታዬ አስጸቀስላሴ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል።
የፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የሥራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል።
አምባሳደር ፕሬዚዳንት ታዬም በምክር ቤቶቹ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን ከቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሣለወርቅ ዘውዴ ጋር ሥራ እርክክብ አድርገዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ መምሪያ የሥራ ክፍል ፣የምዕራብ አውሮፓ ዋና ክፍል ኃላፊ፣የኢንፎርሜሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር፣ስቶክሆልም የኢፌዲሪ ኤምባሲ በአማካሪነት፣በዋሽንግተን የኢፌዲሪ ኤምባሲ በአማካሪነት እንዲሁም በሎስ አንጀለስ ቆንስል ጀነራል፣ በ1998 ዓ.ም ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡
በሎስአንጀለስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ማዕረግ የቆንስላ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ በአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል፣ በ2008 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነውም ሰርተዋል።
በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ተጠሪ ሆነውም አገልግለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው የሰሩት አምባሳደር ታዬ በአሁኑ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በማገልገል ላይ እንደነበሩ ይታወቃል።
ላለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት በX ወይም በቀድሞው ትዊተር ገጻቸው ላይ “ዝምታ ነው መልሴ” የሚል ጽሁፍ ማጋራታቸው ይታወሳል።
ዝምታን “ለአንድ ዓመት ሞከርኩት” ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ምን ደርሶባቸው እንደከፋቸው፣ ለምን እንደከፋቸው እና ለምን ዝም እንዳሉ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያጋሩት ጽሁፍ የግላቸው እንጂ የጽህፈት ቤቱ እንዳልሆነ መናገሩ አይዘነጋም።