ኢትዮጵያ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ አነሳች

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ለመዋዕለ ህጻናት ወይም ኬጂ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዳይማሩ ከልክላ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኬጂ ተማሪዎች እንዳይማሩ አግዶት የነበረውን እንግሊዘኛ ቋንቋ በድጋሚ እንዲሰጥ መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ቢሮው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ ክልከላ የጣለው ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በሚል እንደነበር በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት ተቋርጦ የነበረው የቅድመ መደበኛ (ኬጂ) የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት፤ በዚህ ሳምንት በተጀመረው የ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በሳምንት ለአምስት ጊዜ እንደሚሰጥ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ያዘጋጀው የእንግሊዘኛ ቋንቋ የተማሪዎች መፅሐፍ እና የመምህራን መምሪያ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተሰራጭቷል።

ሕጻናት ወደ አንደኛ ክፍል ከመሸጋገራቸው አስቀድሞ ባለው ቅድመ መደበኛ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የእንግሊዘኛ ትምህርት የተቋረጠው፤ በ2016 ዓ.ም. አዲስ ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) መተገበር በመጀመሩ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የቅድመ መደበኛ ሥርዓተ ትምህርት፤ ከዚህ ቀደም ለ“ኬጂ” ተማሪዎች ትምህርት ሲሰጥ የነበረበትን መንገድ የቀየረ ነበር።

ትምህርት ቢሮ እገዳውን መጣሉን ተከትሎ ወላጆች እና መምህራን እንግሊዘኛ ቋንቋን ያገለለው አዲሱ መመሪያ በካሪኩለም ያልተደገፈ፣ ለመምራን ተገቢው ስልጠና ሳይሰጥ እና የወላጆችን ፍላጎት ያላማከለ ነው በሚል ቅሬታቸውን ተናግረው ነበር፡፡

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፤ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በሌሎች ደረጃዎች እንደሚደረገው ሒሳብ፣ ሳይንስ፣ ቋንቋ በሚሉ የትምህርት ዓይነቶች እንዳልተከፋፈለም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በላይ የቆየውን የትምህርት ስርዓት ወይም ካሪኩለም በመቀየር ላይ ስትሆን የትምህር ጥራት መውደቅ፣ የተማሪዎች እውቀት ማነስ፣ የመማር ፍላጎት መቀነስ እና ብሔራዊ ፈተና ውጤት መቀነሱ ዋነኞቹ ምክንቶች ናቸው፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑት 684 ሺህ 205 ተማሪዎች መካከልም 36 ሺህ 409 ተማሪዎች ብቻ የማለፊያ ውጤት አምጥተዋል፡፡

ወደ ዩንቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት አጠቃላይ ተማሪዎች ከተፈተኑት ውስጥ 5 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ እንዳላሳለፉ ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *