በአማራ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም ተባለ

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በየጊዜው የተኩስ ልውውጥ የሚስተዋልበት አማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዘገብ አቅዶ ነበር፡፡

ይሁንና ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ የተመዘገቡት ተማሪዎች 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ” ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 292 ሺሕ በላይ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 1.2 ሚሊዮን በላይ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ 180 ሺሕ ተማሪዎች ተመዝግበዋል ” ብሏል፡፡

” በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምዝገባው እየተካሄደ ነው፡፡ ትንሽ እሱ ላይ መዘግየት ይታያል፡፡ እስካሁን በጠቅላላ ወደ 1.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ናቸው የተመዘገቡት የእቅዱን ወደ 24 ፐርሰንት አካባቢ ” ነው ያለው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በአማራ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንት ባለፈው ዓመት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ” በክልሉ ከ10 ሺሕ 874 በላይ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የእኛ ፍላጎት እነዚህ ሁሉም ትምህርት ቤቶች 7 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዲያስተምሩ፣ መማር ማስተማሩ እንዲጀምር እና እንዲቀጥል ነው ” ብለዋል፡፡

” በተለይ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጸጥታ ችግር ስላለ የትምህርት ሥራን ከዚህ በፊት እንደምናደርገው ሁሉ የምዝገባ ሥራን ለመስራት እንቅፋቶች ቢኖሩም ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ የምዝገባ አፈጸጻሙ በምንጠብቀው ልክ ባይሆንም ምዝገባ እየተካሄደ ነው ” ሲሉ አቶ ጌታው ተናግረዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱ እዳይደነቃቀፍ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም ሰው ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ቢሮው አስምሮበታል።

” አንድንድ ቦታ ላይ ትላንት ትምህርት ሲጀምሩ ልንማር ይገባል የሚል ሞቶ ሁሉ ይዘው የወጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ ይሄ በጣም ልብ ይብራል ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ሁሉ፡፡ ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ በዛኛው ወገን ያሉ ወንድሞቻችንም ጭምር ይህን ተረድተው ትምህርትን ነጻ ሆነን እንድንስራ በጎ ሚናቸውን መጫወት አለባቸው ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

” በ2016 ዓ/ም በተለያየ ምክንያት ትምህርት ተቋርጦባቸው የቆዩ አካባቢዎች፤ ሳይማሩ የቆዩ ተማሪዎች፤ ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶች አሉ ” ሲልም ቢሮው ገልጿል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ ካለው የጸጥታ ችግር ወይም ግጭት ጋር በተያያዘ 1115 ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ እና መካከለኛ ጉዳቶች እንደደረሰባቸው ተገልጿለ፡፡

በክልሉ በ2016 ዓ/ም መመዘገብ ከነበረባቸው 6.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ርቀው ቆይተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *