በሀገር ክህደት ወንጀል የሞት ፍርድ ተወስኖባቸው የነበሩ 178 ወታደሮች በይቅርታ ተለቀቁ

ወታደሮቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና አመራሮች የነበሩ ሲሆን አዲስ አመትን አስመልክቶ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል

ከሶስት ዓመት በፊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ የሰሜን እዝ በህወሃት ታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይህ ያልታሰበ ጥቃት እንዲደርስባቸው አቀነባብረዋል የተባሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና አመራሮች በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ነበር፡፡

እነዚህ 178 ወታደሮች በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው የእድሜ ልክ እና ሞት ፍርድ ውሳኔ ተላልፎባቸው በእስር ላይ ነበሩ፡፡

በእስር ላይ የነበሩት የሠራዊት አባላቱ በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው የይቅርታ ጥያቄአቸውን ለመንግስት እና ለመከላከያ ሚኒስቴር አሥገብተዋል ተብሏል።

ወታደሮቹ የይቅርታ ጥያቄ ማስገባታቸውን ተከትሎ በአንድ በኩል ጉዳያቸው ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀፅ 3 ድንጋጌ መሰረት ይቅርታ ማድረግ የሚያሳካቸውን አላማዎች ግምት ከማስገባት ሌላ እነዚህ የሰራዊት አባላት በፈፀሙት ወንጀል መፀፀታቸውንም ተመልክቷል።

መንግስት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ይበልጥ ለማፅናት ቁርጠኛ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርዱን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአዲሱ አመት በመታረም ላይ የነበሩ 178 የሠራዊት አባላት ከእስር በይቅርታ እንዲለቀቁ መወሰኑን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ለሁለት ዓመት በዘለቀው በዚህ ጦርነት አንድ ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን አማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልል ደግሞ የጦርነቱ ዋነኛ ሰለባዎች ነበሩ፡፡

የፌደራል መንግስት በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን ለመካስ፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሽግግር ፍትህ ስርዓት የሚተገበርበት ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም እስካሁን ወደ ተግባር አልገባም፡፡

ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ሊቆም ችሏል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በሰራው ጥናት መሠረትም ያጋጠመው አጠቃላይ የጦርነት ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ገልጿል።

በዚሁ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ፣ ‹‹ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 5.5 በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ (Economic Loss)›› መድረሱን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በዚህ ውስጥ ምክንያትም ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት የከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።

በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡

መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው ይህ ጦርነት በሰላም ስምምነት ቢጠናቀቀም ከአንድ ዓመት በፊት በአማራ ክልል ሌላ ጦርነት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ይህ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች እንዲገደሉ ምክንያት የሆነ ሲሆን ለከ10 ወራት በላይ የዘለቀ የኢንተርኔት ገደብ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያትም ሆኗል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም ሀገራት ጦርነቱ እንዲቆም፣ ልዩነቶችም በድርድር እንዲፈቱ በተደጋጋሚ በማሳሰብ ለይ ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *