በሁለት አመቱ የትግራይ ጦርነት የተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ጥሪ አቀረበ።
የያለፈው ጦርነት እና ጥፋት ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ሐይሎች ለሌላ ጥፋት እየተዘጋጁ ነው በማለት አረና ከሷል።
በወቅታዊ የትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ የሰጠው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ለትግራይ አደጋ ይዞ የሚመጣ እና ሐላፊነት የጎደለው አካሄድ እየተከተለ ያለ ሲል ገልፆታል።
የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ “አሁንም ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶች እየታዩ ያሉት እና የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰመው ባለፈው 2 ዓመት ለነበረው ጦርነት ከሁሉም ወገን ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ ነው፤ ከህወሓት ይሁን ከሻዕብያ እንዲሁም ብልፅግና ወገን የጦርነቱ ተጠያቂዎች ስላልቀረቡ አሁንም የጦርነት ፍላጎት አለ ብለዋል።
ዓረና እንደሚለው የህወሓት አመራሮች ልዩነታቸው የግል እና የቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ፍጥጫ የወለደው ነው ብሎ እንደሚያምን የገለፀ ሲሆን ይህ የህወሓት የውስጥ ጉዳይ ሊሆን እየተገባው ሆን ተብሎ ክፍፍሉ ወደ ህዝብ ለማውረድ ብሎም የከፋ ግጭት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብሏል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ የሰሜን እዝ በህወሃት ታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
ለሁለት ዓመት በዘለቀው በዚህ ጦርነት አንድ ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን አማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልል ደግሞ የጦርነቱ ዋነኛ ሰለባዎች ነበሩ፡፡
የፌደራል መንግስት በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን ለመካስ፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሽግግር ፍትህ ስርዓት የሚተገበርበት ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም እስካሁን ወደ ተግባር አልገባም፡፡
ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ባሳለፍነው ጥቅምት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ሊቆም ችሏል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ በሰራው ጥናት መሠረትም ያጋጠመው አጠቃላይ የጦርነት ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ገልጿል።
በዚሁ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ፣ ‹‹ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 5.5 በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ (Economic Loss)›› መድረሱን ሪፖርቱ አመልክቷል።
በዚህ ውስጥ ምክንያትም ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት የከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።
በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡