ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ያሉ የዲፕሎማሲ ተቋማት በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን እንዳያስገቡ ከለከለች

ኢትዮጵያ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን እንዳያስገቡ እገዳ ጥላለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ዲፕሎማቲክ እና ሚሲዮኖች የነዳጅ መኪናዎችን እንዳያስገቡ እገዳ የጣለች ሲሆን በምትኩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስመጣት ብቻ እንዳለባቸው አሳስቧል።

የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ እና የቆንስላ ሚስዮኖች፣ ለቀጠናው እና ለአለም አቀፍ ድርጅቶች በፃፈው ደብዳቤ ” የተወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልዕቀት ቅነሳና ወደ ታዳሽ ኃይል ለመሸጋገር ካላት ቁርጠኝነት የተነሳ መሆኑን” አስረድተዋል ።

በዚህም የዲፕሎማሲ መብት ያላቸው ሁሉ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተሰጠውን አቅጣጫ አክብረዉ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ብቻ ማስመጣት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2016 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ የሚሰሩ የግል አገልግሎት ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ እገዳ መጣሏ ይታወሳል፡፡

መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ የግል ተሽከርካሪዎችን ያገደው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የነዳጅ ወጪውን ለመቀነስ መሆኑን ገልጿል።

መንግስት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የባትሪ መኪናዎችን እንደሚያበረታታና እንደሚያስፋፋም ሚንስትሩ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ተሸከርካሪ እንዳለ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳይ ሲሆን አብዛኞቹ ለዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ናቸው፡፡

ከአረጁ  ተሸከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ለመከላከል ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ አገልግሎት የሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ተጥሎባቸዋል፡፡

እንዲሁም አዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ መኪና አስመጪዎች ደግሞ ዝቅተኛ ግብር እንዲከፍሉ በመደረግ ላይ ሲሆን በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ አዲስ ተሸከርካሪዎች ደግሞ የበለጠ የግብር እና ሌሎች ማበረታቻዎችን ያገኛሉ፡፡

ይሁንና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከል ባለሃብቶችንና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ይጎዳል በማለት ተቃውሟል፡፡

ኮሚሽኑ ለትራንስፖርት ሚንስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ የሕግ ድንጋጌ ሳይኖርና ግልጽ ሕግ ሳይወጣለት ከበላይ አካል በተሰጠ ትዕዛዝ ብቻ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ማገድ አግባብነት የለውም በማለት ቅሬታውን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።

በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተላለፈው ውሳኔ በግብርና፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በአበባ እርሻ ልማት፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግና ግንባታ እና ሌሎች ስራዎች በተሠማሩ ባለሃብቶች እና ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ አክሎም ለአንዳንድ ኢንቨስትመንት ስራዎች ከባሕሪያቸው አንጻር በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዲያስገቡ እንዲፈቀድላቸው ሲል እንደጠየቀም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ከታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *