በጎፋ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ ይችላል ተባለ

በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በደረሰው ተከታታይ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ባወጣው የሁኔታዎች መግለጫ ላይ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አሃዝ እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል አመልክቷል።

እሁድ ሐምሌ 14 እና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተቀብረው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ ዛሬም ለአራተኛ ቀን እየተካሄደ ነው።

በአደጋው ስፍራ ዛሬን ጨምሮ በአካባቢው እየጣለ ባለው ዝናብ ውስጥ ጭምር ከተንሸራተተው መሬት ስር ለማውጣት የሚደረገው የነፍስ አድን ጥረት ቀጥሏል።

ባለፉት ቀናት በተደረጉት የፍለጋ ጥረቶች በአደጋው ሕይወታቸው አልፎ የተገኙ ሰዎች ቁጥር 257 የደረሰ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ስጋታቸውን መግለጻቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አመልክቷል።

በኢትዮጵያ መሰል የመሬት መንሸራተት አደጋ በተለይም በደቡባዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለመደ ሲሆን ይህን ህል አደጋ ሲያጋጥም ግን የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

አደጋው መጀመሪያ ሶስት ቤተሰብ ላይ መድረሱን ያስታወቁት በገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ፤ ይህንን ሰምተው እነሱን ለማዳን ጥረት እያደረጉ እያለ ድጋሚ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ የበርካቶች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።

በአደጋው ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል የወረዳው ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሴቶችና ሕፃናት እንደሚገኙበትም የወረዳው አስተዳዳሪ አስታውቀዋል።

ተጨማሪ የሞቱ ሰዎች አስከሬንን ለማውጣት የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንዲደረግለት የፌደራል መንግስትን ጠይቋል፡፡

ከፍተኛ የክልል እና የፌደራል መንግስታት ባለስልጣናት አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ በመጓዝ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር 50 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ስፍራው ልኳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *