ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ ነበር፡፡
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቋል፡፡
የተገኘው ገቢ ባለፈው በጀት ዓመት ከተገኘው 3 ነጥብ 64 ቢሊየን ዶላር የ4.6 በመቶ ወይም በ166 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው፡፡
ከተገኘው ገቢ የግብርናው ዘርፍ 76 በመቶ በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን ማኑፋክቸሪንግ ማእድን ፣ኤሌክትሪክና ሌሎች በተከታታይ የሚገኙ ናቸው።
ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከ3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ ከውጭ ሀገራት ግዢ በመፈጸም ለተጠቃሚዎች እንደተሰራጨም ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቧ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሀና አርዓያ ስላሴ እንዳሉት ሀገሪቱ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ውስጥ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር መሳቧን ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ 329 የኢንቨስትመንቶች ፕሮጀክቶች ውስጥም 227ቱ የውጭ ባለሀብቶች ሲሆኑ ቀሪው ደግሞ በሽርክና እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ዘንድሮ የተገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ብልጫ ሲኖረው በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ 4 ነትብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብ እንደታቀደ ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡
የቡና ንግድ፣ ማዕድናት፣ የአበባ፣አትክልት እና ፍራፍሬ ንግድ ቅናሽ ከታየባቸው የውጪ ንግዶች መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ ህገወጥ ንግድ፣ የሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት የጸጥታ ችግሮች መባባስ ለገቢ መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡
የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ውስጥ 350 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁንና አፈጻጸሙ 298 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ሀገራት የምትልከው ቡና በቀይ ባህር በኩል በመሆኑ እና የሀውቲ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት መስጓጎል ገጥሞት እንደነበርም ተገልጿል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኤምሲ መርከብ በኩል ወደ አውሮፓ ሀገራት በመጓጓዝ ለይ እያለ በሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት ምክንያት የቡና ንግድ እስከ ሶት ቀናት ድረስ በመስተጓጎሉ ምክንያት ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ ማግኘት የነበረባትን ገቢ እንዳታገኝ አድርጓል፡፡
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀጣይ የቡና ንግድ ላይ ስጋት ሊደቅኑ እንደሚችሉ፣ ነጋዴዎች ምርቶች በወደቦች ላይ ሲቆዩ ለተጨማሪ ወጪ እንዲሁም ይህን ሽሽት ቡናን በአየር ትራንስፖርት ሲልኩ ላልተፈለገ ወጪ ሊዳርጋቸው እንደሚችልም አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የቡና ምርቶቿን ወደ 65 የዓለማችን ሀገራት ልካለች የተባለ ሲሆን ከተላከው ጠቅላላ ቡና ውስጥ 21 በመቶው ወደ ሳውዲ አረቢያ እንደተላከ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ ጃፓን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከላከችባቸው ዓለማችን ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡