በሃጅ ጉዞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ1300 አለፈ

በዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ1300 ተሻግሯል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስቱ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ሳዑዲ አረቢያ ገልጻለች፡፡

በዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ 300 መሻገሩን ሳዑዲ አረቢያ አስታውቃለች።

እስካሁን በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የ10 ሀገራት ዜጎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ 658ቱ ግብጻውያን ናቸው ተብሏል።

150 ሺህ ሃጃጆችን የላከችው ፓኪስታን 58 ዜጎቿ ህይወታቸው ማለፉን ይፋ አድርጋለች።

ከ240 ሺህ ኢንዶኔዥያውያን ሃጃጆች መካከልም 183ቱ መሞታቸውን የሀገሪቱ የሃይማኖቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የሱዳን፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ ህንድ፣ ዮርዳኖስ፣ ማሌዥያና ኢራን ዜግነት ያላቸው ሃጃጆችም ህይወታቸው ማለፉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ከዚህ ውስጥ አምስቱ ኢትዮጵያዊን እንደሆኑ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገልጿል፡፡

አብዛኛዎቹ ሟቾች ያለፈቃድ ወደ አገሪቱ ገብተው በከፍተኛ ሙቀት ረጅም ርቀት የተጓዙ ምዕመናን ናቸው ተብሏል።

የዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የተካሄደው በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ወቅት ሲሆን የሙቀት መጠኑ ከ50 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ የሆነበት ጊዜ ነበር።

ከሟቾቹ ውስጥ ከሦስት አራተኛ በላይ ፍቃድ ሳይኖራቸው የገቡ እና በቂ መጠለያ ሳይኖራቸው በጠራራ በፀሐይ ሲጓዙ የነበሩ ናቸው ሲል የሳዑዲ አረቢያ የዜና ወኪል ኤስፒኤ አስነብቧል።

ከሞቱት መካከል አንዳንዶቹ አረጋውያን ወይም ሥር የሰደደ ሕመም የነበረባቸው መሆናቸውን ኤጀንሲው አክሎ ገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፋህድ አል-ጃላጄል ስለ ሙቀቱ አደገኛነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ሃጃጆች ይህንን እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ከ140 ሺህ በላይ ፍቃድ የሌላቸውን ጨምሮ የጤና ተቋማት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተጓዦችን ማከም የቻሉ ሲሆን አንዳንዶች አሁንም ሙቀቱ ባደረሰባቸው ጉዳት ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል።

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የውጭ እና ከ300 ሺህ በላይ የሳኡዲ ዜጎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ሀጂ በከፍተኛ ሙቀት ተፈትኗል።

የሀገሪቱ የሜቲዮሮሎጂ ማዕከልም ባለፈው ሳምንት የመካ ሙቀት 51 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴልሺየስ መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።

በዚህም እድሜያቸው የገፋና የተለያዩ ህመሞች ያሉባቸው ከ2 ሺህ 700 በላይ ሃጃጆች ሆስፒታል ገብተው እየተካከሙ እንደሚገኙ ተገልጾ ነበር።

ሚሊየኖች በሚሳተፉበትና ከእስልምና አምስት ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የሃጂ ስነስርአት መጠኑ ይለያይ እንጂ በየአመቱ የሃጃጆች ሞት ይመዘገባል።

ከስምንት አመት በፊትም በሚና ጠጠር ውርወራ ሲካሄድ በተፈጠረ መረጋገጥ ከ2 ሺህ በላይ ሃጃጆች ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *