ለስምንት ሳምንታት ያህል ማመልከቻዎችን ሲቀበል ከቆየ በኋላ፣ ሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያ (Reach for Change Ethiopia) በዛሬው ዕለት የማስተርካርድን ኤድቴክ ፕሮግራም የመጀመሪያውን ዙር የተቀላቀሉትን 12 የኤድቴክ ሥራ ፈጣሪዎች ይፋ አድርጓል።
“ኤድቴክ” (EdTech) በእንግሊዝኛው ትምህርት እና ቴክኖሎጂን አጣምሮ የያዘ ቃል ሲሆን፣ ትምህርትን አሳታፊ በሆነና ምቹ መንገድ ለማቅረብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምን የሚገልጽ ሐሳብ ነው።
ፕሮግራሙ የሪች ፎር ቼንጅ እና የማስተርካርድ ፋውንዴሽን አጋርነት አንድ አካል ሲሆን፣ የአጋርነቱ ዓላማም ለተመረጡ የኤድቴክ ድርጅቶች ቁልፍ የሆነ የቢዝነስና የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ፕሮግራሙ ለድርጅቶቹ አዲስን ነገር ስለ መማር ሳይንስ፣ ስለ እድገትና መስፋፋት፣ ስለ ዘላቂነት እንዲሁም ተጽዕኖ ስለ መፍጠር ምልከታን የሚያስጨብጥ ይሆናል።
“እነዚህ ፕሮግራሙን የተቀላቀሉ 12 የኤድቴክ ድርጅቶች የትምህርቱን መስክ ለመለወጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው ብለን እናምናለን።
ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በአጋርነት በመሥራት እነዚህ ድርጅቶች ፈጠራ የታከለባቸውና አካታች የሆኑ የኤድቴክ ምርቶችና መፍትሔዎችን በስፋት እንዲያቀርቡ እናግዛለን።
ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ተማሪዎች የሚገጥማቸውን የትምህርት ክፍተት ለመሙላት ያግዛል። በዚህ አጋርነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ልጆችና ወጣቶች ያሏቸውን ልዩ ልዩ መሻቶች በማሟላት ለአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽዖ ለማበርከት ቆርጠን ተነሥተናል” ሲሉ የሪች ፎር ቼንጅ የኢትዮጵያ ማናጀር መቅድም ጉልላት ያስረዳሉ።
የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኤድቴክ ፕሮግራም በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 36 ፈጠራ የታከለባቸው የኤድቴክ ድርጅቶችን ለማገዝ ያለመ ሲሆን፣ በየዓመቱ 12 ድርጅቶችን እያከለ የመሄድ እቅድ አለው።
ፕሮግራሙ ሴት ልጆችን፣ ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉ ተማሪዎችን፣ ልጆችን እና የአካል ጉዳተኛ ወጣቶችን ጨምሮ አነስተኛ ተደራሽነት ያላቸው የኅበረተሰብ ክፍሎችን መድረስ ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህንን በማድረግ፣ የትምህርቱ መስክ ያለውን አሳታፊነት ለማሳደግ ያልማል።
በመጀመሪያው ዙር ፕሮግራሙን የሚቀላቀሉት 12 የኤድቴክ መፍትሔ አቅራቢዎች መካከል፡-
- አኀዝ ፕላትፎርምስ (Ahaz Platforms PLC) በዋናው ፕሮጀክቱ “አኀዛዊ” በኩል የትምህርት እኩል ተደራሽነትን ለማምጣት የተነሣ ነው። “አኀዛዊ” ዲጂታል የመማሪያ ፕላትፎርም ሲሆን ትምህርት መጀመርን አዳጋች የሚያደርጉትን እንቅፋቶች በመቅረፍ ዘላቂና ወጥ የሆነ የማስተማር ሂደትን ለማሻሻል የሚያስችል ነው።
- ዲናሞ ሴንተር ፎር ቴክኖሎጂ (Dynamo Center for Technology) እንደ ተማሪው የግል ሁኔታ ተስማሚ ተደርገው የሚቀርቡ ኦንላይን የመማሪያ መሣሪዎችንና መፍትሔዎችን የሚያቀርብ ሲሆን፣ በዚህም በከተማና ገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ከፍተኛ ጥራት ባላቸው መገልገያዎች በመድረስ የትምህርት ተደራሽነት ክፍተትን ለመሙላት ይሠራል።
- እንጫወት ጌምስ (Enechawet Games) አሳታፊ የሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ ትምህርታዊ መጻሕፍትን የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከ4 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ላላቸው ልጆች የሚሆን ለአጠቃቀም ምቹ የሞባይል መተግበርያ በመሥራት ላይ ይገኛል።
- ፊደል ቱቶሪያል (Fidel Tutorial) በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ለሚገኙ ተማሪዎች በአካልም ሆነ በኦንላይን የማስጠናት አገልግሎት ይሰጣል። ትኩረቱ ቁልፍ የሆኑ የትምህርት ዓይነቶችን መሸፈንና ለብሔራዊ ፈተናዎች ማዘጋጀት ሲሆን፣ ቅደመ ምዘና፣ ኦንላይን ክትትል እና ከፍተኛ ክህሎት ያላቸው የአስጠኚዎችን ስብስብ ያቀርባል።
- ግሎብ ዶክ (Globe Dock) ለተማሪዎች እንደ ሁኔታቸው ተስማሚ ትምህርት ለማቅረብ ዲጂታል ይዘትን፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ግብዓት ያደረገ ትምህርትን እና መረጃን መሠረት ያደረገ ምልከታን ይጠቀማል። ፕላትፎርሙ ተማሪዎችን በንቃት የሚያሳትፉ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን፣ ትምህርትን እንደ ተማሪው ሁኔታ አስማምቶ በማቅረብ ተማሪዎች ለማኅበራዊ ለውጥ የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ አቅም ይሰጣል።
- ኮደርላብ ማሠልጠኛ ማዕከል (Koderlab Training Center) በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት አቅርቦት ውስንነት ላይ የሚሠራ ነው። የሶፍትዌርና የሃርድዌር ሥልጠና፣ ኦንላይን ክፍለ ጊዜዎች፣ እንዲሁም የተማሪዎችን አቅም የሚያሳድጉና ቁልፍ ዲጂታል ክህሎቶችን የሚያስጨብጡ ሥልጠናዎችን ያቀርባል።
- ኩራዝ ቴክኖሎጂስ (Kuraz Technologies) በኢትዮጵያ የሚታየው የትምህርት አቅርቦት እኩልነት መጓደል እና የማስተማሪያ ዘዴዎች ኋላ ቀርነት ላይ አተኩሮ ይሠራል። ይህንን የሚያደርገውም በዋጋ ተመጣጣኝ፣ ተደራሽ፣ የተማሪውን የግል ሁኔታ ያገናዘበ፣ እንዲሁም አካታች የሆነ ድጋፍ ያላቸውን ሁሉን አቀፍ የኤድቴክ ፕላትፎርሞች በማቅረብ ነው።
- ሙያ ስፔስ (Muya Space) በኢትዮጵያ ለሚገኙ ልጆች፣ ወጣቶች እና የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ክህሎት ያስጨብጣል። አሳታፊ በሆነው ኦንላይን ፕላትፎርሙ፣ ተማሪዎችን በቪዲዮ ክፍለ ጊዜዎችና በቀጥታ ምልልስ በሙያው ከተካኑ አስተማሪዎች ጋር ያገናኛል።
- ሙያሎጂ (Muyalogy) የተማሪውን የግል ሁኔታ ባገናዘበ የትምህርት ሥርዓቱ እና እንደ ሁኔታው አመቺ ተደርገው በሚቀረጹ ኮርሶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለውን የክህሎት ክፍተት በመሙላት ላይ ይገኛል። ለዚህም ሶፍትዌርን እንደ አገልግሎት የሚያቀርብና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ ኦንላይንም ሆነ ያለ ኢንተርኔት ለመጠቀም የሚቻል የመማሪያ ፕላትፎርም የሚጠቀም ሲሆን፣ የቋንቋና የባሕል ልዩነቶችንም ማስተናገድ ያስችላል።
- ቀለም የትምህርት ፕላትፎርም (Qelem Education Platform) የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ከፍተኛ የፈተና ውድቀት መጠን በመቅረፍ የኢትዮጵያን ትምህርት ሁኔታ ለመለወጥ የተነሣ ነው። ፕላትፎርሙ እንደ ሁኔታው ተስማሚ የቪዲዮ ትምህርቶችን፣ ፈተናዎችን እና ማጥኛ ግብዓቶችን በማቅረብ ለተማሪዎች ተስማሚ ኦንላይን መማሪያ አማራጭ ይዟል።
- ሶፍትኔት ሶሉሽንስ (Softnet Solutions) በሚጠቀመው “ፓይ” የትምህርት ሲስተም አማካይነት የኢትዮጵያን ትምህርት ቤቶች ለማሻሻል ያለመ ነው። ትኩረቱም በእጅ የሚሠሩ ተግባራትን በማዘመን ትምህርትን በተለይ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች ይበልጥ አመቺ ማድረግ ነው።
- ዊዝ ኪድስ (Whiz Kids) የሚያቀርበው “ፀሐይ ለቤተሰብ” የተሰኘው ፕሮግራም በኦንላይን ኮርሶች፣ የቲቪና ሬድዮ ዝግጅቶች እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎቶች አማካይነት ሁሉን አቀፍ የልጆች እድገትን ያግዛል።
“ከሪች ፎር ቼንጅ ጋር ባለን አጋርነት በኩል፣ በኢትዮጵያና አፍሪካ የሚገኙ በቂ ዕድል የተነፈጋቸው ተማሪዎች ይበልጥ ጥራትና ፋይዳ ባለው ትምህርት ተደራሽ እንዲሆኑ እየሠራን እንገኛለን።
ይህንን የምናደርገውም እዚሁ በተዘጋጁና ቴክኖሎጂን በሚጠቀሙ መፍትሔዎች ነው። በ2023 እ.ኤ.አ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኤድቴክ ፕሮግራም አጋሮች በደቡብ አፍሪካ፣ በናይጄሪያ እና በኬንያ 2.6 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመድረስ ችለዋል።
በዚህ ዓመት ደግሞ ከዛም ከፍ ያለ ተደራሽነትን እንጠብቃለን” ሲሉ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፈጠራ የታከለበት ማስተማርና መማር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጆሴፍ ንሴንጊማና ይገልጻሉ።
ሦስት ዓመት በሚዘልቀው አጋርነት የተመረጡት የኤድቴክ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያገኙ ሲሆን፣ ድጋፎቹም ለአንድ ዓመት ከዘርፉ ባለሙያ ጋር የአንድ ለአንድ ሥልጠና፣ የአቻ ለአቻ መማማሪያ ክፍለ ጊዜዎች፣ የኢንቨስተር ማማከር አገልግሎት፣ የካርኒጌ ሜለን ዩኒቨርሲቲ መመህራን የሚጠቀሟቸው ኮርሶችን የማግኘት ዕድል፣ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ድርጅት ከድርጅቱ ድርሻ ወይም አክሲዮን የማይጠየቅበት የ60 ሺሕ ዶላር ድጋፍ ተካትተዋል።