ዳሸን ባንክ ለሶስተኛ ጊዜ የዳሸን ከፍታ የስራ ፈጠራ ውድድርን ሊጀምር ነው                                                                                 

ዳሸን ባንክ በስራ ፈጠራ ዘርፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየተገበረ ያለው ዳሸን ከፍታ የስራ ፈጠራ ውድድር ለሶስተኛ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል፡፡

ባንኩ ውድድሩን ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድ በአማካሪነት ከቀጠረው ዊቬንቸር ሆልዲንግስ ከተሰኘ ሃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት እንዲሁም የሚዲያ አጋር ከሆነው የአፍሪካ ሬኔሳንስ ቴሌቪዥን (አርትስ ቲቪ) ጋር ዛሬ በዋናው መስሪያ ቤት ስምምነት መፈራረሙን ለኢትዮ ነጋሪ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የዘንድሮው ውድድር በባህር ዳር፣ ደሴ፣ መቀሌ፣አዳማ፣ድሬዳዋ፣ወላይታ፣ ሃዋሳ፣ጅማ እና አዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በነዚህ ከተሞች በባንኩ ቅርንጫፎች የሰልጣኞች ምዝገባ ከሰኔ 18 እስከ ሰኔ 29-2016 ዓ.ም ይከናወናል፡፡

ለተመዘገቡ ሰልጣኞች በስራ ፈጠራ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል ስልጠና በነዚህ ከተሞች ከተሰጠ በኋላ ሰልጣኞቹ የፈጠራ መነሻ ሃሳባቸውን በፅሁፍ በባንኩ ቅርንጫፎች በኩል እንዲያቀርቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በዚህም መሰረት የተመረጡ ተወዳዳሪዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ ተጨማሪ ስልጠና ወስደውና በሌሎች ተያያዥ መርሃ ግብሮች እንዲሳተፉ ከተደረጉ በኋላ ለውድድር ዝግጁ ይሆናሉ፡፡

ስልጠናውም ተወዳዳሪዎቹ የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን እንዴት መሸጥ እንደሚችሉና የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ወደገበያ ማቅረብ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የውድድሩ አሸናፊዎች ከዕውቅና እና ሽልማት በተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡

ዳሸን ባንክ እስካሁን ባካሄደው በዚህ የስራ ፈጠራ ውድድር በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር በሺዎች የሚቆጠሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች በስልጠና እና ውድድር መርሃ ግብሮች ተሳትፈዋል፡፡

ባለፉት አመታት በተከናወኑት የዳሽን ከፋታ የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ወጣቶችም በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተውና የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎላቸው ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ለሌሎች ወጣቶች ጭምር የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *