በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት መንግስት ታህሳስ እና ግንቦት ላይ በፈጸማቸው ሁለት የድሮን ጥቃቶች 10 ሰዎች ሲገደሉ ከ10 በላይ ቆስለዋል ብሏል፡፡

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በሶማሊ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ባወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ሲሆን አሁንም ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል እጅግ አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ የመብት ጥሰቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ኮሚሽኑ በጸጥታ ችግር እና ከመንግስት ተገቢውን ትብብር ባለማግኘት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የዘገዩ ምርመራዎች በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጾ እስካሁን ያረጋገጣቸውን ጥሰቶች ይፋ አድርጓል።

በርካታ ንጹሀን ዜጎች በመንግስት እና በታጠቁ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን መንግስት ታህሳስ ላይ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በዚህ ወር መጀመሪያ አማራ ክልል ውስጥ በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች አስር ሰዎችን ገድሎ ከአስር በላይ ሌሎችን ማቁሰሉን ተቋሙ በምርመራዬ አረጋግጫለሁ ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን የመተግበር ሂደት ሥልጣንን አላግባብ ለመጠቀም እና ከሕግ አግባብ ውጭ የሆኑ የጅምላ እስሮችን፣ ግድያዎችን፣ ኢ ሰብአዊ አያያዝን እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመፈጸም ክፍት እንዳይሆን የመከላከልና የማስተካከያ ሥራ እንዲሠራ፣ እንዲሁም ተገቢው የሕግ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ኮሚሽኑ ጠይቋል።

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉና የሰብአዊ መብቶች እንዲሁም የሰብአዊነት ሕጎችን እንዳይጥሱ ጥሪ ቀርቧል። 

በክልሎቹ ባሉት ግጭቶች የተሳተፉ ላይ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር፤ እንዲሁም በግጭቱ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተይዘው ተዓማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ከእስር እንዲለቀቁ፣ የመንግሥት የጸጥታና የአስተዳደር አካላት በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ግለሰቦችን በመደበኛ ማቆያዎች ብቻ እንዲይዙና ሁልጊዜም የተያዙ ሰዎች ያሉበት ቦታና ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው እንዲገለጽ፣ እንዲሁም ለተፈናቃዮች ትኩረት እንዲሰጥም የመብቶች ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።

ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።

ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት ቀርቶታል።

በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ምዕራባዊያን ሀገራት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቅሰዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *