በዋሸንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ስለሺ በቀለ የስልጣን መልቀቂያ አስገብተዋል
በአሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ አምባሳደር ሽለሺን ይተካሉ ተብሏል
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ከተሾሙበት የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ምንጮች ገለጹ።
ስለሺ በቀለ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ሹመታቸው ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት መዋቅር በመልቀቅ በግል ተቀጥረው በሙያቸው ለማገልገል ማቀዳቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
አምባሳደር ስለሺ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ወቅት የፓርቲ አባል ሳይሆኑ የመንግሥት መዋቅርን መቀላቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚያ አስቀድመው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በውኃ ምኅንድስና ሙያቸው በግል ተቀጥረው ሲያገለግሉ ነበር።
ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ አምባሳደርነታቸው በመልቀቅ ወደ ቀደመ የግል ሥራቸው ለመመለስ መፈለጋቸውን ተናረዋል የተባለ ሲሆን ጥያቄያቸውንም ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት ማገኘቱን ገልጸዋል።
አምባሳደር ስለሺ በቀለ መልቂቂያ ስለማቅረባቸውና መልቀቂያውም ተቀባይነት ማግኘቱን በመጥቀስ መረጃውን እንዲያረጋግጡ የጠየቅናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
የቀድሞው የአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ መምህር ስለሺ በቀለ በአምባሳደርነት ከመሾማቸው በፊት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሆነው ከአምስት ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡
አምባሳደር ሽለሺ በታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ውይይቶችንም በመምራት ይታወቃሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ዋሸንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሲያገለገሉ የቆዩትን ስለሺ በቀለን የሚተኩት የወቅቱ የሳዑዲ ዐረቢያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
የሌንጮ ባቲ የአሜሪካ አምባሳደርነት ሹመት ዜና የመጣው አምባሳደር ስለሺ በቀለ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ማግኘታቸው ከተነገረ በኋላ ነው።
አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሳዑዲ አምባሳደርነት የተሾሙት በ2013 አጋማሽ ነበር።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በአማካሪነት፣ በኋላ ደግሞ በአምባሳደርነት እያገለገሉ የሚገኙት ሌንጮ ባቲ፣ የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንደኛው ክንፍ አመራር ነበሩ።