ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተለያዩ ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አብርሀም በላይ (ዶ/ር) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ተሸመዋል፡፡
እንዲሁም አይሻ መሀመድ በአብርሀም በላይ ምትክ የሀገር መከላከያ ሚንስትር እንዲሁም የዲያፖራ ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበሩት መሀመድ እንድሪስ (ዶ/ር) በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ተደርገው ተሹመዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር ሽግሽግ ለምን እንዳደረጉ በይፋ ያላሳወቁ ሲሆን በአማራ ክልል የሚገነቡ የመስኖ ግድቦች በወቅቱ አለመጠናቀቃቸውን እና የገንዘብ ብክነት ማጋጠሙን ጉብኝቱን ባካሄዱበት ባሳለፍነው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ደህንነት እና ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ የአመራር ሽግሽግ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ አምባሳደር የነበሩት ታዬ አጽቀስላሴ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
እንዲሁም ዶክተር መቅደስ ዳባ ደግሞ ከጤና ሚኒስትርነት ሀላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ላሰገቡት ዶክተር ሊያ ታደሰ ምትክ ሆነው ተሾመዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የደህንነት አማካሪ የነበሩት ሬድዋን ሁሴን ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይረክተር ተሹመዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ከመስራታቸው በፊት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኢታ፣በኤርትራ እና አየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡
ትዕግስት ሃሚድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንደተሸሙም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከሶስት ወራት በፊት ስልጣን የለቀቁት አቶ ደመቀ መኮንን ላለፉት 11 ዓመታት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከሶስት ዓመት በፊት ደግሞ አቶ ደጉ አንዳርጋቸውን ተክተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሀላፊነትን ይዘው ቆይተዋል፡፡