የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች መመዝገቢያ ጊዜን አራዘመ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ቀሪ ምርጫ በሚደረግባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ በሚደረግባቸው በጅግጅጋ 2 እና መስቃንና ማረቆ ምርጫ ክልሎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም.  ምርጫ ለማከናወን የተለያዩ ዝግጅቶችን  በማድረግ ላይ ይገኛል።

ቦርዱ ከሚያዝያ 21 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት የመራጮች ምዝገባ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

ነገር ግን የመራጮች ምዝገባ በወጣበት የጊዜ ሰሌዳ ወቅት ተደራራቢ የህዝብና የሃይማኖት በዓላት የነበሩ በመሆኑ፣ የመራጮች ምዝገባ የሚደረግባቸው አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ ባለመከፈታቸውና በምርጫ የሚወዳደሩት የፓለቲካ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ ቀን እንዲራዘም በመጠየቃቸው ቦርዱ የመራጮችን የምዝገባ ቀን እስክ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ማራዘሙን አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ  የእጩዎች ምዝገባ ከሚያዝያ 21  እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ/ም  የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት በምርጫው መወዳደር የፈለጉ  ዕጩዎች  ምዝገባ ማካሄዱን ገልጿል::

ይሁንና የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዕጩዎቻቸውን በተለያዩ  ምክንያቶች ማስመዝገብ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ለእጩዎች ምዝገባ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጥያቄ መጠየቃቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

በዚሁ መሰረት ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥያቄ በመቀበል የእጩዎችን የምዝገባ ጊዜ እስከ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ/ም ማራዘሙን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6 ኛውን ዙር ቀሪና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ በሚካሄድባቸው አራት ክልሎች ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ምርጫ የሚካሄደው በጸጥታ እና በሌሎች ምክንያቶች ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ነው የተባለ ሲሆን የቤንሻንጉል ጉምዝ፤ አፋር፤ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 29 የምርጫ ክልሎች ውስጥ እንደሆነም ቦርዱ አስታውቋል፡፡

በዚህ ምርጫ ፕሮግራም ለዘጠኝ የተወካዮች ምክር ቤትና ለሃያ ስድስት የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ለማካሄድ እንደታቀደም ተገልጿል፡፡

በአራቱ ክልሎችም የምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ/ም እንደሚካሄድ ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ አክሎም የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ሰኔ 6 እና ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ/ም፣ ጊዚያዊ ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ማሳወቅ ሰኔ 9 እና ሰኔ 10 2016 ዓ/ም ሲሆን የመጨረሻ እና  በቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ጊዜ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ/ም መሆኑን ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡

በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በአማራ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ያልተካሄደ ሲሆን ክልሉ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ምክንያት በቀሪ ምርጫ ክልሎች ምርጫው አይካሄድም ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደ ሲሆን ክልሉ ያካሄደው ምርጫ በቦርዱ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫን ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አምስት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ አራት፣ በኦሮሚያ የተወዳደሩ ሦስት የግል ዕጩዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ ዕጩ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል የጌዴኦ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት መቀመጫዎችን አግኝተው ነበር፡፡

በአጠቃላይ በሁሉም የምርጫ ክልሎች 39 ሚሊዮን መራጮች ሲመዘገቡ 847 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አስታውቋል፡፡

በዚህ ምርጫ አሸንፈው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል አምስቱ በእስር ላይ ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *