ኦቪድ ግሩፕ እና የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክትን አጠናቀዋል፡፡
ኦቪድ ግሩፕ እና የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ታሪካዊ በሆነ ትብብር በኮዬ ፈጬ የገነቡትን የቤት ፕሮጀክት አጠናቀው አስረክበዋል፡፡
በ16 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና ዘመናዊ የሆኑ የመኖሪያ ቤት አገልግሎቶችን አሟልተዋል የተባሉት እነዚህ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጥራታቸውን ጠብቀው መገንባታቸው ተገልጿል፡፡
ኮዬ ፈጬ አካባቢ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ አራት G+7 እና ሦስት G+9 ሕንጻዎችን፤ በድምሩ ሰባት ሕንጻዎችን የያዘ ሲሆን፤ 120 ባለ ሦስት መኝታ እና 128 ባለ አራት መኝታ፤ በአጠቃላይ 248 የመኖሪያ ቤቶች አሉት።
ግንባታው ወደ የትኛውም ሕንጻ የሚያደርሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እና ለምለም አረንጓዴ ቦታዎችን ያካተተ እና የኑሮ ደረጃን ትኩረት አድርጎ፤ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆን ታስቦ በልዩ ሁኔታ ንድፍ የወጣለት ነው።
1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የፈጀውና በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አማካሪነት የተገነባው ይህ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የከተማ አኗኗርን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሻሽሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማስፈጸም በኩል የኦቪድ ግሩፕን አፈጻጸም ያሳያልም ተብሏል፡፡
መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጀመረውና ይህ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ርክክቡ ተፈጽሟል፡፡
በፕሮጀክቱ መሳካት ደስታቸውን የገለጹት የኦቪድ ግሩፕ ሊቀ-መንበርና የግሩፑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ታደሰ “ከመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ጋር አብረን መሥራታችን ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ሥራዎችን ለመሥራትና ለዘመናዊ ከተማ ግንባታ ያለንን ቆራጥነት አጉልተው የሚያሳዩ የቤት መፍትሔዎችን እንድናቀርብ አስችሎናል።
የሀገራችንን ጀግኖች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው መኖሪያ ቤቶች ባለቤት የሚያደርገውን ይህን ፕሮጀክት ገንብተን በመጨረሳችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል።
ኦቪድ ግሩፕ የከተማ ኑሮን የሚያሻሽሉ ዘላቂ እና ዘመናዊ አካባቢዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለ እና የሪል ስቴቶች ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም የሆነ ቡድን ነው።