ኢትዮጵያ ምዕራባዊ ሀገራት በቡድን መግለጫ እንዳስፈራሯት ገለጸች

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ 18 ምዕራባውያን ሀገራት ኢምቢሲዎች ‘የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን’ አስመልክተው ባሳለፍነው ሳምንት ባወጡት የጋራ መግለጫ የኢትዮጵያን የጋዜጠኞች አያያዝ ተችተዋል።

በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር ከጠየቁ ሀገራት መካከልም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ ቤልጂየም፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ኔዘርላንድ እና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡

ሀገራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ስራቸውን በመስራታቸው “ማስፈራሪያ እና እስር ይደርሰባቸዋል” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰውም ነበር።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ምዕራባዊን ሀገራት በቡድን መግለጫ በማውጣት ሊያስፈራሩኝ ሞክረዋል ስትል አስታውቃለች፡፡

“ኢትዮጵያ መግለጫውን ካወጡት እያንዳንዳቸው ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አላት፣ ግንኙነታችን የሚመራው በዚህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ በቡድን ማውጣት እንደ ማስፈራራት ይቆጠራል” ብለዋል አቶ ነብዩ።

የአውሮፓ ህብረት መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ ተባባሪ አይደለችም በሚል ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት የጎደለው እንደሆነም ተገልጿል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት “የአውሮፓ ህብረት 86 ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጉ ሲሉን መጀመሪያ እነዚህ ዜጎች ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን በሚል ባደረግነው ማጣራታም 26ቱ ብቻ ኢትዮጵያዊ ሆነው ተገኝተዋል” ብለዋል።

በአውሮፓ ሀገራት ይኖሩ የነበሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ካላገኙ መካከል 15 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አቶ ነብዩ ተናግረዋል።

ይህን ሁሉ ጥረት እያደረግን ህብረቱ ኢትዮጵያ ተባባሪ አልሆነችም በሚል በኢትዮጵያውያን ቪዛ አመልካቾች ላይ የቪዛ ገደብ መጣሉ አግባብ ነው ብለን እናምንም ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።

በአውሮፓ ህብረት አዲስ የቪዛ ገደብ ውሳኔ መሰረት የቪዛ ማመልከቻ ጊዜን ከ15 ቀናት ወደ 45 ቀናት ከፍ ያደረገ ሲሆን ቪዛው ለአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ እንዲሆንም ወስኗል።

የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ እንዳሉት ከሰሞኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር ስላስተባበለው የትግራይ ታጣቂዎች ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ጋር ተሰልፈው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎችን እየወጉ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በምላሻቸው ጉዳዩን እንደሰሙ ነገር ግን እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊያን ታጣቂዎች በሱዳን ጦርነት ውስጥ መሳተፍ አለመሳተፋቸው እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

“ታጣቂዎቹ በሱዳን ጦርነት መሳሰተፍ አለመሳተፋቸው ከተጣራ በኋላ መረጃውን ይፋ እናደርጋለን” ሲሉም አቶ ነብዩ በምላሻቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የዓለም ፕረስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ያወጡት መግለጫ ነው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *