የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገኘ

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተጓዦችና የጭነት አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

ማኅበሩ በየቀኑ ከ7 መቶ እስከ 1ሺህ ሰዎችን የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ155 ሺህ በላይ ተጓዦችን እና 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የጭነት አገልግሎት በማጓጓዝ የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከ13 እስከ 15 በመቶ የወጪና ገቢ ምርት የሚያጓጉዘውን ማኅበር ከፈረንጆቹ 2024 ጥር ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ የማስተዳደር ኃላፊነት ወስዳ እየሰራች መሆኗን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በባቡር ትራንስፖርት ምቹ ምኅዳር በመፍጠርም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የገቢና ወጪ ምርት የማጓጓዝ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ከ1ሺህ በላይ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት በማጓጓዝ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት እየደገፉ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት የሁለቱን ሀገራት ዜጎች በማገናኘት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

ከ2009 ጀምሮ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ውስጥ ሶስት ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጾ ነበር።

752 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከፈረንጆቹ ጥር 2018 ጀምሮ የመንገደኞች እና የእቃ ማጓጓዝ ትራንስፖርት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የባቡር መስመር ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ 70 በመቶው ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር 30 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ መገንባቱ ይትወሳል።

የዓለም ባንክ ለኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር 730 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ታወሳል፡፡

የ730 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነቱን ገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ ለአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት (በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ፕሮጀክት) ባሳለፍነው ነሀሴ ተፈራርመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን 90 በመቶ የባህር ንግድን የሚይዘው ስትራቴጂካዊው ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ኮሪደር ጋር በተሳሰረ መልኩ የኢትዮጵያን የሎጅስቲክስና የትስስር አቅም እንደሚያጎለብት ተጠቁሟል።

በስምምነቱ መሰረት ለሜኦሶ -ድሬዳዋ መንገድ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፤ ግንባታው የትራንስፖርት አቅምና ብቃት የሚጨምር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መንገዱ በሚገነባባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች የጤና፣ ውሃና ትምህርት አገልግሎት ተደራሽነት ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ድጋፍ እንደሚደረግም ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ አካልና የቀጣናዊ ትብብር ማዕቀፍ እንደሆነ ያመለከተው ሚኒስቴሩ፤ ማዕቀፉ አካባቢውን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ፋይዳም እንዳለው ተጠቅሷል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *