ኢትዮጵያ ከ18 ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ዜጎችን አባረረች

የተባረሩት የውጭ ሀገራት ዜጎች ህጋዊ የነዋሪነት ፈቃድ የሌላቸው እንደሆኑ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

ዳይሬክተሯ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በሐሰተኛ የመኖሪያ ፍቃድ በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ18 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎችን ከአገር እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡

ከአገር ከተባረሩት የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል የተወሰኑት ሐሰተኛ የመኖሪያ ፍቃድ አዘጋጅተው በገንዘብ ሲሸጡ የነበሩ እንደሚገኙበት ተቋሙ አስታውቋል፡፡

በኢንቨስትመንት ፍቃድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የውጭ ዜጎች ለበርካታ ዓመታት በሕገወጥ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ኾነው እንደተገኙም ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ከዚህ በፊት በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀሰተኛ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ሀሰተኛ ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ሀሰተኛ ፓስፖርት፣ ሀሰተኛ ቪዛ እና ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲኖሩ እንደነበር አስታውቋል፡፡
እነዚህ የውጭ ሀገራት ዜጎች ከመባረራቸው በፊት ሀሰተኛ ማስረጃ ይዘው በኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች እንዲመዘገቡ እና ትክክለኛ የነዋሪነት ፈቃድ እንዲያገኙ በተደጋጋሚ ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛን ወይም ቪዛ ኦን አራይቫል አገልግሎትን ከመስከረም ወር ጀምሮ በመስጠት ላይ መሆኗ ይታወሳል።

ዋና ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸው ላይ የፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በኤርፖርቶች እና የየብስ መውጫ ድንበሮች ላይ ያሉ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መሻሻል ቢኖሩም አሁንም ሀላፊነታቸውን የማይወጡ ሰራተኞች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሚል አገልግሎት ፈላጊዎችን የሚያንገላቱ፣ ጉቦ የሚጠይቁ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመጠቀም አገልግሎት የሰጡ 44 ሰራተኞችን በህግ እንዲጠየቁ መደረጉም ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *