ኢትዮጵያ የየነዳጅ ፍላጎቷን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ሀገራት በመግዛት የምትሸፍን ሲሆን የትራንስፖርት ዋጋ እንዳያንር በሚል የነዳጅ ድጎማ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
የመንግስት ወጪ በመጨመሩ እና የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት የነዳጅ ድጎማን ቀስ በቀስ ለመቀነስ እና ለማቆም እንደወሰነች የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው ዓመት ይፋ አድርጓል፡፡
የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማይሰጡ ድርጅቶች የነዳጅ ድጎማው ከቆመ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን አሁን ደግሞ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም የነዳጅ ድጎማ እንደማያገኙ ተገልጿል፡፡
ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ ሲደረግላቸው የነበሩ የሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ድጎማው እንደሚቋረጥ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል።
መንግሥት ለረጅም ጊዜ ለነዳጅ ምርቶች ከፍተኛ መጠን የለው ድጎማን ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ ይህንን ለማስቀረት በሂደት የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ባወጣው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ቀስ በቀስም መንግስት በነዳጅ ምርት ላይ የሚያደርገዉ ድጎማ የማቋረጥ እቅድ እንዳለዉ ይታወቃል፡፡
በሚኒባስ ተሸከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረገዉ መንግስት ድጎማን የማስቀረቱ አንዱ አቅድ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ሆኖም የድጎማ ስርአቱን የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች ማህበረሰቡን በሚገባ እያገለገሉ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሰልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሄኖስ ወርቁ ከዚህ ቀደም 170ሺ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ስርአት ውጪ መደረጋቸዉን ተናግረዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ነዳጅ ድጎማን በስርዓት ባለመጠቀማቸው እና ህግ እና ስርዓትን ተከትለው አልሰሩም በሚል ከድጎማው ውጪ እንዲደረጉ ምክንያት መሆኑ አመላክተዋል።
ከፊታችን መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጅምሮ በነዳጅ ድጎማው ስርአት የሀገር አቋራጭና የከተማ አውቶቢስ ብቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀው እነዚህም ተሽከርካሪዎችን እስከሚቀጥሉት 5 አመታት ብቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡
በነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን በኩል ከመጋቢት 30 2016 ዓ.ም በኃላ ድጎማዉ ከሚኒባስ ተሸከርካሪዎች ላይ እንደሚያነሳ የተወሰነ ቢሆንም ተግባራዊ የሚደረገዉ ግን የነዳጅ አገልግሎት ስርጭትን በተመለከተ ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክ፤ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባላድርሻ አካላት የተዉጣጣዉ ኮሚቴ ዉሳኔዉን ሲያሳልፍ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርገግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት ከታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዢ ማውጣት እንደማትችል ገልጸው ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስመጡ እና በሀገር ውስጥ መገጣጠም እንዲጀምሩ መንግስትም ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ያገደች ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስገቡ ወይም በሀገር ውስጥ እንዲገጣጥሙ እስከ35 በመቶ የግብር ቅናሽ እንደሚደረግላቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡