ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ አገደች

ከወራት ማመንታት በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ የግል አገልግሎት ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ እገዳ መጣሉ ተገልጿል፡፡

መኪኖችን ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ስራ የተሰማሩ ኩባንያዎች እንዳሉት ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ተናግረዋል።

ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከአውሮፓና ደቡብ አፍሪቃ ያጓጓዟቸውን በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ማስገባት እንደማይችሉ ከሶስት ሳምንት በፊት ተነግሯቸዋል። በእገዳው ሳቢያ ከፍተኛ መጉላላትና ኪሳራ እንደደረሰባቸው ባለጉዳዮቹ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል።

ከሳምንታት በፊት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ማገዱን ለፓርላማ አባላት ሲያስታውቅ የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ እገዳው ተገባራዊ እንደማይደረግና በዕቅድ ደረጃ ያለ መሆኑን ተናግሮ ነበር።

ይሁንና ባለፉት ቀናት የተለየ ፍላጎት ላላቸው የልማት ፕሮጀክቶችና ለህዝብ ትራንስፖርት የሚውሉ ካልሆኑ በቀር በነዳጅ የሚሰሩ የግል ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ታግደዋል።

“እንዲህ አይነቱ አሰራር ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ዝግጅት እንድናደርግና ከውጪ ተጭነው በመንገድ ላይ ያሉና የውጪ ምንዛሪ የወጣባቸውን ተሽከርካሪዎች እንድናስረክብ ዕድል መሰጠት ነበረበት” ይላሉ በከተማዋ በአስመጪነት ስራ የተሰማሩ ባለሀብት።

በመጪው ሳምንት ከትራስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር ማቀዳቸውንም እኝሁ አስመጪ ተናግረዋል።

በውጪ ሀገር ከሀያ ዓመታት በላይ የቆየ ሌላ ግለሰብ ደግሞ አቅሜ የሚፈቅደውን አይነት ለግል መገልገያ ተሽከርካሪ ገዝቼ አስፈላጊውን የጉምሩክ መስፈርት ባሟላም፣ መኪናውን ማስገባት እንደማልችልና ወደመጣበት እንድመልሰው ተነግሮኛል ብሏል።

መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ የግል ተሽከርካሪዎችን ያገደው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የነዳጅ ወጪውን ለመቀነስ መሆኑን ገልጿል።

ከሰሞኑ ለመንግስት ሚዲያዎች መግለጫ የሰጡት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚንስትሩ አለሙ ስሜ የነዳጅ መኪና ክልከላው ተግባራዊ መደረግ መጀመሩንና መንግስት የኤሌክትሪክ መኪና ላይ ከፍተኛ የቀረጥ ማበረታቻ ማድረጉን አረጋግጠዋል።

መንግስት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የባትሪ መኪናዎችን እንደሚያበረታታና እንደሚያስፋፋም ሚንስትሩ አብራርተዋል።

ሚንስትሩ አክለውም ህብረተሰቡ በነዳጅ የማይሰሩ የትራንስፖርት አማራጮችንና የእንስሳት እና ብስክሌት እንዲጠቀሙ ብሎም በእግሩ መጓጓዝን ልማድ እንዲያደርግ መክረዋል።

ሚኒስቴሩ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውሉና የተለየ ምክንያት ላላቸው የግል ላልሆኑ ተቋማት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን እንዳማይከለክል አለሙ ስሜ ጠቁመዋል።

ይህ አሰራር የሀገሪቱ የአረንጓዴ ልማት አንድ አካል መሆኑንና “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጪነት” በካቢኔ ውይይት ተደርጎበት ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረም ሚንስትሩ አመልክተዋል።

በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪናዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ተከትሎ በሀገር ውስጥ ስላሉት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ምን ዕቅድ እንዳለው መንግስት አላሳወቀም።

በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ተሸከርካሪ እንዳለ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳይ ሲሆን አብዛኞቹ ለዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ናቸው፡፡

ከአረጁ  ተሸከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ለመከላከል ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ አገልግሎት የሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ተጥሎባቸዋል፡፡

እንዲሁም አዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ መኪና አስመጪዎች ደግሞ ዝቅተኛ ግብር እንዲከፍሉ በመደረግ ላይ ሲሆን በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ አዲስ ተሸከርካሪዎች ደግሞ የበለጠ የግብር እና ሌሎች ማበረታቻዎችን ያገኛሉ፡፡

በዓለም ላይ በአየር ብክለት ምክንያት ከሚደርስ የሰዎች ሞት ውስጥ 11 በመቶ ያህሉ ከተሽከርካሪዎች በሚወጣ በካይ ጋዝ ምክንያት እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *