በአማራ ክልል በጦርነት እና ድርቅ ምክንያት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ተገለጸ

በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር እና ድርቅ ምክንያት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን በክልሉ ያለው የጸጥታ እና ድርቅ ችግሮች በተማሪዎች ምዝገባ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብለዋል።

ክልሉ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር ሲገባው ያን ማድረግ አለመቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል።

ከሁለት ነጥብ 6 ሚሊዮን ያልተመዘገቡ ተማሪዎች መኖራቸውን የገለፁት ኃላፊው ፤ መማር የሚገባቸው ተማሪዎች የትምህርት ዕድል እንዳያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

ከ2015 ዓ/ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ የሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት መከሰቱ ይታወሳል፡፡

ይህ ጦርነት እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ በክልሉ ከሀምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም፡፡

በጸጥታው ችግር ምክንያት ሁለት ሺህ በሚጠጉ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ከመማር ማስተማር ሥራ ውጪ የሆኑ ሲሆን መምህራኑ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ባለው ግጭት “ወደ 42 ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውንም” ጠቁመዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ መንግሥት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ክልሉ እና በክልሉ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት በጋራ ይሠራሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት ዙሪያ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳለው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በተለምዶ ፋኖ በመባል ከሚታወቀው አካል ጋር ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ ጦርነት በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለ ሲሆን በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች እንዲያመልጡ ተደርጓል የሚለው ኢሰመኮ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎም አሳሳቢ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡

የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ፣ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከ200 በላይ የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

የአስገድዶ መደፈር ወንጀሉ ከተፈጸመባቸው አካላት መካከልም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች እና የጤና ባለሙያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል ተብሏል።

በክልሉ ያሉ በርካታ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ለወታደራዊ አገልግሎቶች እየዋሉ ነው ያለው ኮሚሽኑ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች የግልሰቦች ንብረቶች ለውድመት እና ዘረፋ መዳረጋቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

በክልሉ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥም ኢሰመኮ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡

በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ሁሉም ቦታዎች ኢንተርኔት የተዘጋ ሲሆን በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጦርነቱ እንዲቆም፣ የተቋረጠው ኢንተርኔት እንዲለቀቅ እና ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *