ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ታንዛኒያን እንደሚጎበኙ ተገለጸ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኬንያ ያመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በናይሮቢ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩ ሲገለጽ የተለያዩ ተቋማትንም ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ኬንያ ሲጓዙ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ እና ኬንያ ከ70 ዓመት በፊት ጀምሮ ጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ከአንድ ሳምንት በፊትም የኢትዮ ኬንያ ሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ አካሂደዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ያለ ቪዛ ወደ ኬንያ እንዲሁም ኬንያዊያን ወደ ኢትዮጵያ ያለቪዛ እንዲገቡ የሚፈቅድ የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኬንያ የገቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ሊወያዩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል የዲፕሎማሲ መካረር ተከስቷል፡፡

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር የምትደራደረው ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት ከሰረዘች ብቻ ነው ስትል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ከኬንያ ቆይታቸው በኋላ ወደ ዳሬሰላም  እንደሚያመሩ የታንዛኒያ ሚዲያዎች እየዘገቡ ናቸው፡፡

የታንዛንያው ዘ ሲቲዝን እንደዘገበው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአርብ ጀምሮ ወደ ታንዛኒያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት የሚያመሩት ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን ግብዣ መሰረት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ኬንያን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሀይል በመሸጥ ላይ ስትሆን ለታንዛኒያም ተጨማሪ ሀይል ለመሸጥ የሁለትዮሽ ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በታንዛኒያ ቆይታቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ሲሆን የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ ስምምነት እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለኬንያ፣ ጅቡቲ፣ እና ሱዳን ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ሽያጭ 47 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የፌደራል ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከሚገዙ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ለዓመታት የተጠቀመችበትን 70 ሚሊዮን ዶላር እዳ አልከፈለችም ተብሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *