በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃ እና ወደራ ወረዳ ሳሲት በተባለች ከተማ ህዝብ ያሳፈረ አይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመው ጥቃት 30 ሰዎች ሲገደሉ 18 ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ከአምስት ቀን በፊት ሳሲት በተባለችው ከተማ አቅራቢያ 50 ሰዎችን ያሳፈረ አይሱዙ ተሽከርካሪ መንገደኞችን ለማውረድ በቆመበት ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት 18 ሰዎች መቁሰላቸውንም ነው የአይን እማኞችን የጠቀሰው የሪሊፍ ዌብ ዘገባ የሚያሳየው።
የድሮን ጥቃቱ ሲፈጸም በአካባቢው በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት እንዳልነበር የተናገሩት ነዋሪዎች፥ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም ድሮኖች በአካባቢው ሲሽከርከሩ እንደነበር ገልጸዋል።
የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው መከላከያ ሰራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ ከሚያደርጉበት አካባቢ በ24 ኪሎሜትር ርቀት ላይ እንደተፈጸመ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
“መጀመሪያ ከባድ ፍንዳታ ሰማን ከዚያም አካባቢው በጭስ እና አቧራ ተሸፈነ፤ የ15 ሰዎችን አስከሬን ሰብስበናል፤ እጅና እግራቸው እዚያም እዚህም የተበታተኑ ሟቾችን አስከሬን መሰብሰብ ዘግናኝ ነበር” ብለዋል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ቄስ በሰጡት ቃል።
በጥቃቱ 10 የቤተሰብ አባላቱን እንዳጣ የሚገልጽ ሌላ የሳሲት ነዋሪም በጥቃቱ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከባድ ፍንዳታ ከመሰማቱ በፊት ትንሽ ድሮን መመልከቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልሉ ግጭት ድሮኖችን በስፋት እየተጠቀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ እስካሁን በጥቂቱ 81 ንጹሃን በድሮን ጥቃት እና ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መንገድ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው መግለጹም አይዘነጋም።
በሰብአዊ መብት ኮሚሽን የቀረቡትን የተወሰኑ ክሶች ውድቅ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት፥ በአማራ ክልል ህግና ስርአትን ለማስከበር እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው በክልሉ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ዙሪያ ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸው ጥያቄ “ህዝብ ላይ የድሮን ጥቃት አንፈጽምም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
“ድሮን የገዛነው ልንዋጋበት ነው፤ እስካሁን ባለን አቅም ልክ ድሮንን አልተጠቀምንም ምርጥ ኢላማ ስናገኝ ህዝቡን በማይጎዳ መልኩ እንመታለን” ሲሉም በክልሉ የድሮን ጥቃቱ እንደሚቀጥል ማብራሪያ መስጠታቸው አይዘነጋም።
ይህ በዚህ እንዳለ ከአንድ ወር በፊት በአማራ ክልል መራዊ ከተማ ከ80 በላይ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት ተገድለዋል የተባለ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ግድያው የተፈጸመው ሰራዊቱ ራሱን ለመከላከል ሲል ነው ብሏል፡፡
በዚህ ግድያ ዙሪያ አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች እና ሌሎች ሀገራት እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ግድያው በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር የጠየቁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል፡፡
በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ጦርነት እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመተዳደር ላይ ይገኛል፡፡
ለስድስት ወራት ታውጆ የነበረው የአማራ ክልል አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎትም ተቋርጧል፡፡